የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጥቁር አንበሳ የአጥንት ሕክምና ሐኪሞች በዶ/ር ነብዩ ኤርሚያስ፣ ዶ/ር ሐብታሙ መንክር እና ሌሎች 9 ሐኪሞች ላይ ትናንት የ12 ቀናት የምርመራ ጊዜ መፍቀዱን የጤና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማ አስተባባሪዎች አስታውቀዋል። ፖሊስ በጤና ባለሙያዎቹ ላይ ያቀረበው ክስ፣ ተጠርጣሪዎቹ በሥራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘታቸው የታካሚዎች ሕይወት እንዳለፈና ተጠርጣሪዎቹ ከአመጸኛ ኃይሎች ጋር ግንኙነት በማድረግ ሽብር ለመፍጠር እንደሞከሩ የሚገልጹ እንደኾኑ አስተባባሪዎቹ ጠቅሰዋል። ክሶቹ “የፈጠሬ ክሶች” ናቸው ያሉት አስተባባሪዎቹ፣ ሁሉም ታሳሪዎች ያለምንም ቅድመ ኹኔታ እስኪፈቱና መንግሥት ለጤና ባለሙያዎች ጥያቄዎች “ተጨባጭ” እና “በጊዜ የተገደበ” መልስ እስኪሠጥ።የሥራ ማቆም አድማው እንደሚቀጥል ገልጸዋል።