ጥያቄ እየጠየቀ ያለን ባለሙያ ለማሸማቀቅ በሚመስል መልኩ እንደማስፈራሪያ መጠቀሙ ከአንድ ትልቅ ኃላፊነት ካለበት ተቋም አይጠበቅም

” ጥያቄ እየጠየቀ ያለን ባለሙያ ለማሸማቀቅ በሚመስል መልኩ እንደማስፈራሪያ መጠቀሙ ከአንድ ትልቅ ኃላፊነት ካለበት ተቋም አይጠበቅም ” – የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኅበር
ከሰሞኑን የጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴ እና እያካሄዱ ካሉት ከፊል የሥራ ማቆም ጋር በተያያዘ 78 የሚሆኑ ባለሙያዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ባለሙያዎቹና የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኀበር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናገሩ።
ጤና ባለሙያዎቹ በሰጡት ቃል፣ ” ቀደሞ ከተፈቱት ውጪ አሁን በእስር ላይ የሚገኙት 78 ጤና ባለሙያዎች ናቸው ” ብለዋል።
” ይሄ ማለት እስከ ትላንት የደረሰን ዳታ ነው፤ የዛሬውን አልጨመርንበትም። የተፈቱትን ሳይጨሞር እንቅስቃሴው ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ ታስረው በእስር የሚገኙ ናቸው ” ብለዋል።
ዳታው በምን መልኩ ተሰበሰበ ? ትክክለኛነቱን በምን አረጋገጣችሁ ? ለሚለው ጥያቄ ” ዳታው ትክክለኛ ዳታ ነው። ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ አብረዋቸው ከሚሰሩ የሆስፒታል ባለሙያዎች የተበሰቡ፣ ያሉበት እስር ቤት ጭምር የምናውቃቸው ናቸው ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኀበር በበኩሉ ፥ በእስር ላይ ይገኛሉ የተባሉት 78 ባለሙያዎች ዝርዝር እንደደረሰው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።
” የታሰሩ ባለሙያዎች ዳታ በውስጥ ከመረጃ መሰብሰቢያ ቋት የደረሰን መረጃ ነው ” ብሏል።
” እስራቱና ድብደባው ቆሞ መንግስት ነገሩን ቆም ብሎ በማሰብ ጥያቄ እየነሳው ካለው ባለሙያው ጋር እልህ በመጋባት ታች ያለው ህብረተሰብ እንዳይጎዳ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ” ሲልም አሳስቧል።
ማኅበሩ የትላንቱን የጤና ሚኒስቴር መግለጫ በተመለከተ በሰጠው አስተያየት ፥ ” ጤና ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ከእውነታው የራቀና ትክክለኛ ጥያቄ እያቀረቡ ያሉ ጤና ባለሙያዎችን ‘በሃሰተኛ መረጃ የተወናበዱ’፣ ‘ምንም አይነት መሰረታዊ ጥያቄ የላችሁም’ ከማለት አይተናነስምና አገላለጹ ልክ አደለም ” ሲል ተቃውሟል።
” ምንም እንኳ በአለም አቀፉ ሰራተኞች ተቋም እና በህገ መንግስቱ የመደራጀትና አድማ የመምታት መብት የተፈቀደ ቢሆንም የጤናው ዘርፍ ወሳኝ እና አድማ ከማይደረግባቸው ተቋማት አንዱ መሆኑን በመግለጫቸው ጠቅሷል ” ያለው ማኅበሩ ” ይህ የተገለጸው የግል ሠራተኞች ላይ በወጣው አሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ላይ የተገለጸ እንጂ በመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ላይ የተቀመጠ አይደለም። ይህ ወሳኝ ነው ከተባለ ታዲያ እዚህ ላይ ለሚሰሩት ጤና ባለሙያዎች ወሳኝ ባይሆን እንኳ እንዴት መሰረታዊ ፍላጎታቸውን በማሟላት አያሳዩም ? ” የሚል ጥያቄ ሰንዝሯል።
” ማንኛውም ጤና ባለሙያ ለማገልገል እስከተማረ ድረስ የሚያገለግልበትን እድል በትክክለኛው መንገድ መፍጠር እየተቻለ ጥያቄ እየጠየቀ ያለን ባለሙያ ለማሸማቀቅ በሚመስል መልኩ እንደማስፈራሪያ መጠቀሙ ከአንድ ትልቅ ኃላፊነት ካለበት ተቋም አይጠበቅም ” ሲል ወቅሷል።
በሌላ በኩል ማኀበሩ፣ ” የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማህበር ቴሌግራም ቻናል ፕሬዝዳንቱ ከታሰረ በኋላ አካውንቱ አማካኝነት ከ5/9/2017 ዓ/ም ጀምሮ ከጤና ባለሙያው ጥያቄ ጋር የማይሄድ ተቃራኒ ሃሳብ እየተንሸራሸረበት ይገኛልና ጤና ባለሙያው ይህን ይገንዘብ ” ብሏል።
ማህበሩ በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 የተቋቋመ መሆኑን በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀፅ 3 ከቁጥር 3 እስከ 4 የጤና ባለሙያዎች መብት እንዲከበርና በጤናው ዘርፍ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር እንዲስተካከል ጥረት እንደሚያደርግ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።
በተያያዘ መረጃ ፥ የኢትዮጵያ ህክምና ተማሪዎች ማህበር በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ በኢንተርን ሃኪሞች ላይ እየደረሰ ያለው አያያዝ እጅግ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።
አንዳንድ ኢንተር ሃኪኮም በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ መሆናቸውን የሚገልጽ ታማኝ መረጃ እንዳለው ጠቁሟል።
ሌሎች ደግሞ የአካዳሚክ ቅጣቶች እና ማስፈራሪያዎችን፣ ዛቻዎችን እያስተናገዱ መሆናቸውን ገልጿል።
ያለው ሁኔታ አስቸኳይ ትኩረት የሚሻ ነው ብሏል።
ማኅበሩ ፤ ኢንተርን ሃኪሞች ከሌሎች የጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን በጤና ሴክተር ውስጥ ስላሉት የስራ ፈተናዎች፣ ደህንነት እና አጠቃላይ የስርዓት ተግዳሮቶች ስጋታቸውን ሲገልጹ መቆየታቸውን አስታውሷል።
ኢንተርን ሀኪሞችን ማሰር በግል ደህንነታቸውና ሙያዊ እድገታቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በህዝብ አገልግሎት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል እንዳልሆነ ጠቁሟል። ጉዳዩ የጤና ስርዓትም እንደሚነካ አስረድቷል።
በመሆኑም ፦
– ከሰላማዊ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ኢንተርን ሃኪሞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣
– በኢንተር ሃኪሞች ላይ የአካዳሚክ ቅጣት ፤ ማስፈራሪያና ዛቻ በአስቸኳይ እንዲቆም፣
– በስልጠና እና በስራ ቦታቸው የጤና ባለሙያዎች ደህንነት እና ሙያዊ ክብራቸው እንዲረጋገጥ፣
– የኢንተርን ሃኪሞች እና ሌሎችም የጤና ባለሙያዎች ህጋዊ እና ሙያዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ ሲል ማኅበሩ አስቸኳይ ጥሪ አቅርቧል።
ጤና ሚኒስቴር ትላንት ባወጣው መግለጫ፣ ” የጤና ሞያ የሥራ ማቆም አድማ ከማይደረጉባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑ በግልጽ ተደንግጓል ” ሲል አስገንዝቧል።
በተጨማሪም ሰሞኑን በስራ ገበታቸው ላይ አልተገኙም ስላላቸው የተወሰኑ ባለሙያዎች ” ” ድርጊቱ የራስን ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ወገን እና መላውን ማኅበረሰብ ከመጉዳት ባለፈ ከሞያ ሥነ ምግባር፣ ከሰብአዊነት አኳያ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ” ብሏል።
ባለሙያዎች ስራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ ያሳሰበው ሚኒስቴሩ ” መንግሥት በሆደ ሰፊነት ችግሩን ለመፍታት ያሳየውን ትዕግሥት ወደጎን በመተው በሥራ ገበታቸው ላይ ባልተገኙ እንዲሁም በጤና ተቋሙም ሆነ ከጤና ተቋሙ ውጭ ሆነው ሁከትና ብጥብጥ በሚፈጥሩት ላይ አስፈላጊ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ” ሲል አስጠንቅቋል።