የኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር፣ ከሥራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ ከ78 በላይ የጤና ባለሙያዎች መታሠራቸውን ገልጸዋል። የሥራ ማቆም አድማው አስተባባሪዎችም፣ የጤና ሚንስቴር በአድማ ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ባስቸኳይ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ያወጣውን ማስጠንቀቂያ አጣጥለዋል። ሚንስቴሩ ሁሉም ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሠጡ እንደሆነ መግለጡን ያስተባበሉት አስተባባሪዎቹ፣ በርካታ ሆስፒታሎች ከፊል አገልግሎት እየሠጡ እንዳልኾነ ገልጸዋል። ሚንስቴሩ በዚህ አካሄዱ ከቀጠለ፣ ሁሉም ጥያቄዎች ምላሽ እስኪያገኙ፣ በእስር ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በሙሉ እስኪፈቱና በጥያቄዎቹ ላይ ድርድር እስኪደረግ ድረድ፣ የጤና ባለሙያዎች ከቀጣዩ ሰኞ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉም አስተባባሪዎቹ አስጠንቅቀዋል።