አይኤምኤፍ መንግሥት በምንዛሪ ለውጡ ምክንያት ለኑሮ ውድነት የተጋለጡትን በበቂ ሁኔታ አልረዳም አለ

ሪፖርተር ፡ በገንዘብ ምንዛሪ ለውጡ ምክንያት ለኑሮ ውድነት የተጋለጡ ዜጎችን ለመታደግ፣ መንግሥት የከተማና የገጠር ሴፍቲኔት ማስፋፋት እንዳለበት፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) አሳሰበ፡፡

ባለፈው ዓርብ ተቋሙ የኢትዮጵያን ሪፎርም ለመደገፍ በሚል 248 ሚሊዮን ዶላር መልቀቁን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአይኤምኤፍ ጋር በተስማማው መሠረት ሪፎርሙን እየተገበረው ቢሆንም፣ መንግሥት እስካሁን በሪፎርሙ ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደጎም እለቃለሁ ብሎ ቃል የገባውን ያህል ገንዘብ አለመልቀቁን ተቋሙ ገልጿል፡፡

ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ እየተተገበረ ያለው የምንዛሪ ፖሊሲ ለውጥ፣ የአንድ ዶላር ዋጋ ከብር ከ57 ወደ 125 ብር በዕጥፍ እንዲያድግ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት በዋጋ ንረት ላይ ጭማሪ እንዲታይ አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት ከምንዛሪ ለውጡ በፊት ከነበረው ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሕዝብ ቁጥር በላይ ለኑሮ ውድነት መጋለጡ ተገልጿል፡፡

የምንዛሪ ለውጡ ከመደረጉ በፊት መንግሥት ከተቋሙ ጋር በተስማማበት መሠረት እንዲህ ዓይነት ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሴፍቲኔትን በከፍተኛ ሁኔታ አስፋፋለሁ ብሎ ቃል መግባቱን የስምምነቱ ሰነድ ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ በሰዓቱ የዋጋ ንረቱ እንደሚኖር ቢተነበይም፣ አይኤምኤፍ ምንዛሪ ለውጡ እንዲደረገ ግፊት ሲያደርግ ከቆየ በኋላ፣ አሁን ችግሩን መናገሩ መፍትሔ እንደማይሆን ተንታኞች ገልጸዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት መንግሥት በምንዛሪ ለውጡ ምክንያት የኑሮ ውድነት በማኅበረሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀልበስ የአገሪቱን ጠቅላላ ምርት (GDP) አንድ ተኩል ከመቶ %) በ2017 ዓ.ም. እመድባለሁ ብሎ የነበረ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ የጂዲፒውን 0.4 ከመቶ ከራሱ በጀት፣ ለሴፍቲኔት የተቀረውን በተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎች በተለይ ነዳጅ፣ መድኃኒትና መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በኩል በድጎማ መልክ አቀርባለሁ ብሎ ነበር፡፡

በዕቅዱ መሠረት መንግሥት በቀጥታ የጥሬ ገንዘብ ዕርዳታ የሚደረግላቸውን ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ቁጥር አሳድጋለሁ የሚል የነበረ ሲሆን፣ አይኤምኤፍ ይህ በወቅቱ አለመደረጉን ገልጿል፡፡

እስከ ዛሬ በሴፍቲኔት በየዓመቱ ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰዎች ገደማ የሚረዱ ሲሆን፣ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር በቅርብ ጊዜ በከፍተኛ ቁጥር መጨመሩን ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ ከመንግሥት በተጨማሪ የዓለም ባንክ፣ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት (USAID) እና ሌችም ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ባለፈው ዓርብ የወጣው ይህ የአይኤምኤፍ ግምገማ እንደሚያሳየው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የተስማማባቸውን አብዛኛዎቹን ጉዳዮች መተግበሩንና አንዳንድ የተጓተቱ መኖራቸውን ጠቅሷል፡፡ ለምሳሌ የብሔራዊ ባንክ የኦዲት ሪፖርት በዚህ ጥር ወር እንዲቀርብ ስምምነት ላይ ተደርሶ የነበረ ሲሆን፣ ቀነ ገደቡ በሁለት ወራት ለመጋቢት መራዘሙን ገልጿል፡፡

ሌላው በስምምነቱ መሠረት ይፈጸማል ተብሎ የነበረው የውጭ ዕዳ ሽግሽግ ሲሆን፣ እሱም እስካሁን ከውጭ አበዳሪዎች ጋር በድርድር ላይ መሆኑን ከመጥቀስ ባለፈ የዘገየበትን ምክንያት ተቋሙ አልገለጸም፡፡ ይሁንና ተንታኞች እንደሚሉት በውጭ ምንዛሪ ለውጡ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ያድጋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የወጪ ንግድ ገቢ እንደተባለው አለመሆኑና የወጪ ንግድ ገቢ ከጠቅላላ ምርት ያለው ጥመርታ (Export to GDP Ratio) አሁንም ዝቅተኛ መሆኑ፣ የውጭ አበዳሪዎች የዕዳ ሽግሽግ ውሳኔውን እንዲያዘገዩ ማድረጉን ይጠቁማል፡፡ የጥመርታው ማደግ ኢትዮጵያ የሚያሸጋሽገውን ዕዳ ወደፊት መክፈል ትችላለች ወይስ አትችልም የሚለውን ውሳኔ ለመስጠት እንደ መመዘኛ ይወሰዳል፡፡

የተቋሙ ግምገማ እንደሚያሳየው የጥቁር ገበያ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱንና ይህም የአገሪቱ የምንዛሪ ክምችት እንዲሻሻል ማድጉን ነው፡፡

ይሁንና አሁንም መንግሥት የበጀት ጉድለትን ለመሙላት ተጨማሪ የአገር ውስጥ ብድርና ተጨማሪ የገንዘብ ሥርጭት ካደረገ የኑሮ ውድነቱን ሊያባብስና ተጨማሪ ዜጎች ከድህነት ወለሉ በታች ሊወድቁ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡