ከህወሓት መሰረዝ በኋላ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እጣፈንታ ምንድነው ?
“ የህወሓት ሙሉ በሙሉ ህጋዊ ሰውነት ማጣት የፕሪቶሪያውን ስምምነት አይሽረውም፡፡ በህወሓት የተፈረመውን የፕሪቶርያ ስምምነት የሚፈፅም አካል በዛው ስምምነት ተወልዷል እሱም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ነው ” – አቶ ያሬድ ኃይለማርያም
የህወሓት ከፓርቲነት መሰረዝና የህግ ባለሙያ አስተያየት !
የህወሓት ጉዳይ ፖለቲካዊ መፍትሔ ነበር የሚያስፈልገው ?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ህወሓትን ከፖለቲካ ፓርቲነት ሰርዞታል።
ይህን አስመልክቶ አንድ የህግ ባለሙያ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡት የህግ ባለሙያውና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ሲሆኑ የህወሓት ጉዳይ በደረቅ ህግ ሳይሆን በፖለቲካዊ መንገድ መታየት ነበረበት ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ ዕድሜ፣ የአመሰራረት ታሪክና ቁመና እንዳላቸው የገለፁት ባለሙያው፣ እነዚህን ፓርቲዎች በአንድ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ በአንድ ህግ ብቻ ማየት ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በራሱ የሕወሓትን እጣፈንታ መበየን ሲገባው፣ ይህን ጉዳይ ጨምሮ ስምምነቱ ያላያቸውና ያልተብራሩ በርካታ ጉዳዮች አሉ ያሉት ባለሙያው፣ ስምምነቱ ጥቅል ጉዳዮችን በቻ የያዘ ስለሆነ፣ በሌሎች ሰነዶች መብራራት ነበረበት በማለት ገልፀዋል፡፡
የህግ ባለሙያው በዝርዝር ምን አሉ ?
” ምርጫ ቦርድ በህወሓት ላይ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ህጉን የተከተሉ ሲሆኑ፣ በህወሓት የሚነሱት ጉዳዮች ደግሞ ፖለቲካዊ ናቸው፡፡
‘ እንደ አዲስ ፓርቲ መመዝገብ የለብኝም፣ ለረዥም ጊዜ የነበረ ፓርቲ ነው፣ እንደነባር ፓርቲ ነው የምንቀጥለው እንጂ ዛሬ እንደሚመሰረት አዲስ ፓርቲ አዲስ ምዝገባ ማድረግ የለብንም ‘ ነው የሚለው ህወሓት፡፡ የህወሓት ጉዳይ መፈታት የነበረበት በፖለቲካ ብቻ ነው፡፡
የህወሓት ጉዳይ የፖለቲካ መፍትሔ ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ደረቅ በሆነ የህግ አንቀፅ ልትፈታው አትችልም፡፡
ህወሓት ዝም ብሎ ቢሮ ብቻ ከፍቶ፣ አባላትን ፊርማ አስፈርሞና አሰባስቦ በምርጫ ቦርድ መመዘኛ ተመዝግቦ የተፈጠረ ድርጅት አይደለም፡፡ ግዛት የያዘ፣ የታጠቀ ሀይል ያለው፣ በትጥቅ ትግል የተፈጠረ ድርጅት ነው፡፡ ለአመታት ማንም ፈቃድ ሳይሰጠው በትግሉ ተመስርቶ ሀገር አስተዳድሮ የመጣ አካል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፓርቲዎች ልዩነት፣ አንዳንዶቹ ግዛት አላቸው፣ የታጠቀ ሀይል አላቸው፣ ሌሎች ደግሞ ቢሮና አባል ብቻ ይዘው የሚቀመጡ ናቸው፡፡ እኩል ቁመና የሌላቸው ተፎካካሪ ሀይሎች ናቸው ያሉት፡፡
የዚህ አይነት የተዘበራረቀና የተለያየ ቁመና ያላቸውን ፓርቲዎች እኩል በአንድ አይነት ህግ ልትዳኛቸው አትችልም፡፡ ምክንያቱም ህጉ እኩል ነው የሚያያቸው፡፡ ባህሪያቸው እና አፈጣጠራቸው ግን የተለያየ ነው፡፡
ስለዚህ ፖለቲካዊ ውይይት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ”
የፕሪቶርያው ስምምነት ጉድለት አለበት ?
” የፕሪቶርያ ስምምነት እስከተፈረመበት ጊዜ ድረስ ህወሓት ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የክልል መንግስትም ነበረ፡፡ የፕሪቶርያው ስምምነት አንዱ ችግር ስለ ቀጣይ ስራዎች በዝርዝር የሚያስረዱ ሰነዶችን ያካተተ አለመሆኑ ነው፡፡
ሁለቱም ፈራሚ አካላት ወድያውኑ ጥሩ ግንኙነት በነበራቸው ሰዓት ላይ መሰራት የሚገባቸው ግን ደግሞ ያልተሰሩ ጉዳዮች አሉ፡፡ በሌሎች ሰነዶች መብራራት የነበረባቸው በርካታ ጉዳዮች ነበሩ፡፡
የፕሪቶርያ ሰነድ ጥቅል ነው፣ ብዙ ነገሮችን ያብራራ አይደለም፡፡ የዛ ስምምነት ቁልፍና ዋነኛ ግቡ ጦርነቱን ባስቸኳይ በማቆም እየተጎዳ የነበረውን ህዝብ ማዳን ነው የነበረው፡፡
በቀጣይ ወደፊት የትግራይ ክልል እጣ ፈንታ፣ የህወሓት እጣፈንታ፣ በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልላዊ መንግስት መካከል ያለው ግንኙነት ከአመት ሁለት አመት በኋላ እንዴት ይሆናል የሚለውን ነገር ያስቀመጠ ሰነድ አይደለም፡፡ እነዚህ ነገሮች በቀጣይ በሰነድ መብራራት ነበረባቸው፡፡ ያ ጥቅል ስምምነት በሌሎች ሰነዶች መደገፍ ነበረበት፡፡
ይህን ሰነድ ሰላም ከተፈጠረ በኋላ መሰራት የነበረበት ነው፡፡ ያኔ ተኩስ እየተካሔደ ይህን ማሰብ አይቻልም፡፡ በሒደት ግን እንዲህ ዓይነት፣ የወደፊት አለመግባባቶችን ሊፈታ የሚችል ሰነድ መዘጋጀት ነበረበት፡፡ ”
በፖለቲካዊ ውሳኔ ልዩ እውቅና መስጠት ይቻል ነበር ?
” ምርጫ ቦርድን ሲመሩ የነበሩት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ‘ በሽብርተኝነት ለተፈረጀ ፓርቲ እውቅና አልሰጥም፣ ነባሩ ህግ አይፈቅድም ‘ ሲሉ፣ በፌደራሉ መንግስት በኩል የፖለቲካ መፍትሔ ነው የተሰጠው።
አዲስ ህግ አውጥተው ወድያውኑ በሽብርተኝነት የተፈረጀ ድርጅት ሰላማዊ መንገድ ከመረጠ ዳግም መመዝገብ ይችላል ተባለ፡፡ ይሄ አንድ የፖለቲካ ውሳኔ ነው የተወሰነው፡፡
ግን ያኔ ፓርቲውን ዳግም ለመመዝገብ መመሪያን ማሻሻል ሳይሆን፣ በቀጥታ ህጋዊ እውቅናውን መመለስ ነበር የሚገባው፡፡ ያኔ የታለፈ ዕድል ይህ ነው፡፡
የህወሓትን እጣ ፈንታ እዛው መወሰን ይቻል ነበር በህግ፡፡ የፖለቲካ አቃፊነት እንዲኖር፣ የህወሓትን ሁኔታ አንድ ተጨማሪ አንቀፅ አካትቶ ያለምንም አዲስ የምዝገባ ሒደት ግን እንደ ማንኛውም ፓርቲ የሚጠበቁበትን ሁኔታዎችና ግዴታዎችን አሟልቶ እውቅናውን በህግ አረጋግጦ በመስጠት መቀጠል ይቻል ነበር።
ከዛ በኋላ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች እንጂ የፓርቲ ህልውና ላይ ጥያቄ አይነሳም ነበር፡፡
ለህወሓት እውቅና የሚሰጥ ህግ በፓርላማ ቢፀድቅ ምርጫ ቦርድ አልቀበልም አይልም፡፡ በዚህ መልኩ ልዩ እውቅና ሰጥተህ፣ ከዚህ በኋላ ግን ‘ እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ህጎች ትተዳደራለህ ‘ ትለዋለህ፡፡ እንደዛ ቢሆን ችግር አይፈጠርም ነበር፡፡
ዛሬ እንደ አዲስ እውቅና እንሰጣሀለን፣ አንሰጥህም የሚለው ክርክር የተሳሳተ የፖለቲካ ውሳኔ የፈጠረው ነው የሚመስለኝ፡፡ ”
የህወሓት በምርጫ ቦርድ መሰረዝ፣ የትግራዩን ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶርያውን ስምምነት እንደማይሽረው የህግ ባለሙያው አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
ህወሓት ስምምነቱን ቢፈርምም በዛው ስምምነት መሰረት የፕሪቶርያውን ስምምነት የሚያስፈፅም ጊዜያዊ አስተዳደር መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
ስምምነቱን በትግራይ በኩል ሲያስፈፅም የነበረው ህወሓት ሳይሆን ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
የሕግ ባለሙያው አቶ ያሬድ ኃይለማርያም በዝርዝር ምን አሉ ?
“ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈረምና ከዚያ በፊት ህወሓት የክልሉ አስተዳዳሪ ነበር፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ግን ህወሓት የክልሉ አስተዳዳሪ አይደለም፡፡ ከስምምነቱ በኋላ ክልሉ የሚተዳደረው በጊዜያዊ መንግስት ነው፡፡ ታጣቂው ሀይልም ከህወሓት እንዲለይ ተደረገ፡፡ ልዩነቱ ይህ ነው፡፡ከስምምነቱ መፈረም በኋላ ክልሉ ሌላ ባለቤት ተሰጠው ማለት ነው፡፡
በትግራይ በኩል ስምምነቱን እንዲያስፈፅም ሐላፊነት የተሰጠውም ለጊዜያዊ አስተዳደሩ እንጂ ለህወሓት አይደለም፡፡
የፕሪቶርያውን ስምምነት የሚያስፈፅም አካል በዛው በፕሪቶርያው ስምምነት አማካኝነት ተፈጥሯል፣ እሱም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ነው፡፡
የክልሉን ሓላፊነት የተሸከመው ህወሓት ሳይሆን በዛው በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት የተፈጠረው የክልሉ ጊዜያዊ መንግስት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ስምምነቱንም ሲተገብር የነበረው ህወሓት ሳይሆን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ነው፡፡
ህወሓት ስምምነቱን ፈርሞ ትግበራውን ለጊዜያዊ አስተዳደሩ አስረክቦዋል፡፡ የፕሪቶርያው ስምምነት የሚተገበረው በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል ነው፡፡ ስለ ፕሪቶርያ ስምምነት አተገባበር ክልላዊ መንግስቱን ወክለው አቶ ጌታቸው ረዳ ነበሩ ማብራሪያ የሚሰጡት፡፡ ሐላፊነቱም እሳቸው የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር ነበር፡፡ አሁን ህወሓት ቢሰረዝም የክልሉ ጊዜያዊ ክልላዊ መንግስት ግን አለ፡፡ ይኸው ጊዜያዊ ክልላዊ መንግስት አሁንም ስምምነቱን ያስፈፅማል /ያከናውናል፡፡
ስምምነቱን የፈረመው አካል ነው ስምምነቱን መተግበር ያለበት የሚባል ነገር የለም፡፡ ያኔም ቢሆን ‘ ስምምነቱን የፈረምኩት እኔ ነኝ መፈፀምም ያለብኝ እኔ እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አይደለም ‘/የሚል ጥያቄ አላነሳም ህወሓት፡፡ አሁንም በፕረዝደንት ታደሰ ወረደ የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ‘ ስምምነቱ ህወሓትን ነው የሚመለከተው እኔ አያገባኝም፣ ስምምነቱንም አልፈፅምም ‘ ብሎ ራሱን እስካላወጣ ድረስ ስምምነቱ ፈርሷል ወደሚል ህጋዊ ሙግት አያስኬድም፡፡ ተፈፃሚነቱ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ይቀጥላል፡፡
ህወሓት ስለተሰረዘ ወድያውኑ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ይፈርሳል የሚል ነገር አያስኬድም፡፡
ስምምነቱ በአጠቃላይ ክልሉ ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ፣ በፌደራሉ መንግስት ስር ሆኖ ክልሉን የሚያስተዳድር ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ወደ ህገመንግስታዊ ስርዓት እንዲመለስ ነው የሚያዝዘው፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ስልጣን የሚመነጨው ከፕሪቶርያው ስምምነት ነው፡፡
በፌደራሉ መንግስት በኩልም ቢሆን ስምምነቱን የፈረመው ብልፅግና መሩ መንግስት ቢሆንም ብልፅግና ከሌለ የፕሪቶርያው ስምምነት አይተገበርም ማለት አይደለም፡፡ ሌላ ስልጣን የያዘ ፓርቲ የኢትዮጵያ መንግስት የፈረመውን ስምምነት ይፈፅማል፡፡ ስምምነቶች እንዲህ በቅብብሎሽ ነው የሚተገበሩት፡፡ ፈራሚ አካል ብቻ ስምምነቱን ይተግብር የሚል ነገር የለም፡፡ ”
የህወሓት መሰረዝ ግን ለስምምነቱ መተግበር እንቅፋት ሊሆን ይችላል ?
“ ያለ ህወሓት ትብብር ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን ስምምነት ማስፈፀም ይችላል ወይ ? የሚለው ጥያቄ እዚህ ጋ ሊነሳ ይችላል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሪቶርያውን ስምምነት ለመፈፀም አቅም ይኖረዋል ወይ፡፡ ለምሳሌ ትጥቅ ማስፈታትን ብትወስድ ህወሓት ታጣቂው ሀይል ትጥቅ አይፈታም ካለ ምንድነው የሚደረገው፡፡ ስለዚህ የስምምነቱ ትግበራ ላይ ችግር ይፈጥራል፣ ምንም ጥያቄ የለውም እንቅፋት ይሆናል፡፡ ”
የፕሪቶሪያ ስምምነት አደጋ ላይ የሚወድቀው መቼ ነው ?
“ የፕሪቶርያው ስምምነት ሊፈርስ የሚችለው፣ ህወሓት ‘ ስምምነቱን አልቀበልም፣ ጊዜያዊ አስተዳደረሩንም አልቀበልም ‘ ቢል ነው፡፡ አሁን ግን ህወሓት እንደዛ አላለም፡፡
የፕሪቶርያን ስምምነትና በዚሁ መሰረት የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር ‘ አልቀበለውም እዚህ ክልል ውስጥ መንቀሳቀስም ሆነ መስራት አይችልም ‘ አላለም፡፡
አደገኛ የሚሆነው ‘ እኔ በፈረምኩት የፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት፣ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ከዛሬ ጀምሮ ፈርሷል፣ በዚህ ክልል መንቀሳቀስ አይችልም፣ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚባል ነገር አንፈልግም ‘ ብለው፣ ልክ ጌታቸው ረዳን እንዳባረሩት፣ ጀነራል ታደሰንም ቢያባርሩትና እሱ ያቋቋመውንም ካቢኔ ካፈረሱት ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ፈርሶ ክልሉ በህወሓት ቁጥጥር ስር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሁሉም ነገር ከስምምነቱ በፊት ወደነበረው ኹኔታ ተመልሷል ማለት ነው፡፡
የፕሪቶርያው ስምምነት የሚያወራው ስለ ህወሓት ቀጣይ እጣ ፈንታ አይደለም፡፡ ነገሮች ወደነበሩበት ይመለሳሉ ሲል ህወሓትም እንደ ማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ይቀጥላል ፤ ክልሉም አስተዳደር ይኖረዋል፣ በፌደራሉ መንግስት ስር ነው የሚለው፡፡
የፕሪቶርያ ስምምነት በክልሉ ሰላም እንዴት ይመጣል፣ በክልሉና በፌደራሉ መንግስት ያለው ግንኙነት እንዴት ወደነበረበት ይመለስ የሚል ነው፡፡
ህገመንግስቱ እውቅና የሚሰጠው ለህወሓት ሳይሆን ለክልሉ ነው። እንደ ማንኛውም ፓርቲ ህወሓት እኮ ከፈለገ ራሱንም ማክሰም ይችላል፡፡ ህወሓት ከምርጫ ቦርድ ጋር ተያይዞ የገጠመው ችግር ራሱን ችሎ የሚታይ ነው፡፡ ”