“የትግራይ ሕዝብ አሳር ሊያበቃ ይገባል መፍትሄ ይሰጥ”- ኢሕአፓ
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ነባራዊ የትግራይ ክልል ሁኔታን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ በበርካታ ችግሮች እየተጨቆነ ያለው የክልል ማህበረሰብ አሳር ሊያበቃ ይገባል ሲል ገልጻል፡፡
በቅርቡ አክሱም ውስጥ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች፣ ሂጃብ በማድረጋቸው የተነሳ በተወሰኑ ርዕሰ- መምህራን የተናጠል ውሳኔ ለፈተና እንዳይ መዘገቡ መደረጋቸውን፣ይህንንህገ-ወጥ የዕምነት ነፃነት ነፈጋን፣ ከህግም ከሀገራዊ እሴቶች ያፈነገጠ በመሆኑ በአጽኖኦት እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡
እንዲሁም ፍርድ ቤት እንዲያርሙ የሰጠውን ትዕዛዝ ለማክበር ፈቃደኞች አለመሆናቸው ደግሞ ከፍተኛ ዕብሪትና ህገ-ወጥነት ስለሆነ በአፋጣኝ በሚመለከታቸው ክልላዊና የፌዴራል ባለሥልጣናት አስገዳጅ የርምት ርምጃ እንዲወስድባቸው ፓርቲው አሳስቧል፡፡
የትግራይ ህዝብ በአንዳድ የመገንጠል ዓላማ ባላቸው ፖለቲከኞች የተነሳ ከጎረቤቱ የአማራና የአፋር ክልል ህዝብ ጋር ሁሌም በጠላትነት እንዲተያይ የሚደረገው የአንዳንድ ፖለቲከኞች ሸር ማብቃት አለበትም ተብሏል፡፡
በመሆኑም ሁለቱም የህወሓት ቡድኖች በንግግርና በመቻቻል አስቸኳይ ሠላማዊ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያበጁ እና በትግራይ ክልል የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በማድረግ የህዝቡ ሁለንተናዊ ሠላም እንዲረጋገጥ መደረግ እንደሚገባው ኢሕአፓ አሳስቧል፡፡
በተጨማሪም ምንም እንኳን የትግራይ ህዝብ እንደ ፌደሬሽን አባልነቱ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት 38 ወንበሮች ያሉት ቢሆንም ከጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ተወክሎ አያውቅም።
ይህም ሲባል ባለፉት 4 ዓመታት በፓርላማው እና በፌደሬሽን ምክርቤቶች የሚተላለፉ ውሳኔዎች የትግራይ ህዝብን ፍላጎቶች ያካተቱ አልነበሩም፤ ስለዚህ ለዚህም አስቸኳይ ምርጫ በማካሄድ የትግራይ ህዝብ ጉዳዮችን በእንደራሴዎቹ እንዲወስን በህዝብ ተወካዮች እንዲወከል እንዲደረግ ጠቁሟል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ፣ በአክሱም ከተማ ትምህርት ቤቶች በሒጃብ ሳቢያ በሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ የተጣለው የትምህርት እገዳ አጀንዳ መኾን አይገባውም ነበር በማለት ገልጸዋል፡፡
ጌታቸው፣ ትናንት በመቀሌ በእገዳው ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ያደረጉ ሙስሊሞች ተወካዮችን ባነጋገሩበት ወቅት፣ ችግሩ “ኾን ተብሎ የተፈጠረ አጀንዳ” መኾኑን መጠቆማቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል።