ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማት አብይ አሕመድ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ እንዲያደርግ አዘዙ

ከስድስት ወራት በፊት የተደረገውን የውጪ ምንዛሪ ለውጡን ከግምት ውስጥ ያስገባ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ እንዲደረግ ከዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጥሪ መቅረቡን ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል።

ጥቂት ወራት በፊት መንግሥት ከፍተኛ የተባለ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ጭማሪ ተግባራዊ ቢያደርግም፣ ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማቱ ግን ተጨማሪ ክለሳዎች እንዲደረጉ እየጠየቁ መሆኑን ጋዜጣው መረዳቱን ጠቅሷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ያፀደቀው የኤሌክትሪክ ታሪፍ ጭማሪ፣ ካሳለፈነው መስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑ ይታወቃል።

አገልግሎቱ በአዲሱ የታሪፍ ማሻሻያው እስከ 200 ሜጋ ዋትስ ሰዓት የሚጠቀሙ ደንበኞችን ድጎማ እንደሚያደርግ መገለፁን ያስታወሰው ዘገባው፣ ማሻሻያው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ደንበኞች ታሳቢ አድርጓል ቢባልም የተደረገው ጭማሪ በዓመት ውስጥ 122 በመቶ መድረሱንም ጠቅሷል።

ይህም ሆኖ፣ ከማክሮ ኢኮኖሚ ለውጡ ጋር በተገናኘ እንደ ዓለም ባንክ እና የዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋምን(አይ.ኤም.ኤፍ) የመሳሰሉት ዓለም ዓቀፍ የአገሪቷ አጋሮች የተለያዩ ድጋፎች ከማድረጋቸው ጋር ተያይዞ፣ መንግሥት ያፀደቀውን የታሪፍ ጭማሬ በድጋሚ እንዲያጤነው መጠየቃቸውን ዘገባው አትቷል።