“የነዳጅ ምርት እጥረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ በመምጣቱ ሽያጩ በኩፖን እንዲሆን ተወስኗል” የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል
በየጊዜው የነዳጅ እጥረት ከመሻሻል ይልቅ እየተባሰ በመምጣቱ ሽያጩ በኩፖን እንዲሆን ተወስኗል ሲል ያስታወቀውየደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ገቢያ ልማት ቢሮ ነው፡፡
በቢሮው በኩል ለሁሉም ዞን ንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ ዛሬ ተጽፎ በተሰራጨው ሰልኩላር ደብዳቤ መሰረት ከጥር 30 ጀምሮ ሁሉም የነዳጅ ማደያ ያለባቸው ከተሞች ከጥር 30/2017 ጀምሮ ነዳጅ በኩፖን እንዲሸጥ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ቢሮው የነዳጅ ምርት እጥረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በተለይ የባለ ሁለት እግር ሞተሮች በየቀኑ ተመላልሶ መቅዳት ለኮንትሮባንድ ሽያጭ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ለችግሩ መባባስ ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸውን ከተደረገው ክትትል ለማረጋገጥ ተችሏል ብሏል።
በአንዳንድ የክልሉ ከተሞች የኩፖን ሥርዓት በመዘርጋቱ ሥርጭት ላይ ያለውን የቤንዚን ምርት በአግባቡ ማሰራጨት መቻሉንና ለክትትልም ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ማስተዋሉን ነው በደብዳቤው የጠቀሰው።
በመሆኑም የነዳጅ ማደያ ያለባቸው ከተሞች ከጥር 30/2017 ዓ.ም ጀምሮ የትኛውም ተሽከርካሪ በኩፖን ብቻ እንዲስተናገድ እና ታርጋ የሌላቸው ተሽከርካሪዎች ሀጋዊ የተሽከርካሪ ሠሌዳ እስኪያወጡ ድረስ የግልም ሆነ የመንግስት ተሽከርካሪዎች እንዳይስተናገዱ ሲል በደብዳቤው ጠቅሷል።
ቢሮው አክሎም “ህገ-ወጥ የሆኑትን ማክሰም አስፈላጊ በመሆኑ ተግባራዊ እንዲደረግ እየገለጽን የነዳጅ ምርት ሽያጭም ቢሆን በኤሌክትሮኒክስ ቴሌ ብር እና ሲቢኢ ብር/ የመገበያያ መንገዶች ብቻ እንዲፈጸም በጥብቅ እናሳስባለን፡፡” ሲል በሰርኩላር ደብዳቤው አስታውቋል።
