አዋሽ አካባቢ እየተከሰተ ያለው የእሳተ ገሞራ ልቀት የአውሮፕላን ጉዞዎችን አቅጣጫ ማስቀየር ጀመረ
(መሠረት ሚድያ)- ላለፉት በርካታ ወራት አዋሽ አካባቢ እየተከሰተ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው የእሳተ ገሞራ እና ተያያዥ የተስፈንጣሪ ልቀት ኢትዮጵያ ውስጥ የአውሮፕላን ጉዞዎችን ማስተጓጎል መጀመሩ ታውቋል።
መሠረት ሚድያ ከአቪዬሽን ምንጮቹ፣ ከፍላይት ራዳር እንዲሁም ከአንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስራ ሀላፊ ማረጋገጥ እንደቻለው እሳተ ገሞራው ወደ አየር እየለቀቀ ያለው አቧራ መሰል ቅንጣት (dust particle) አውሮፕላኖች ጉዟቸውን እንዲቀይሩ ማስገደድ ጀምሯል።
“እስከ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ድረስ በዚህ ምክንያት መስተጓጎል ነበር” ያሉት የአየር መንገድ ምንጫችን አሁን ላይ ስላለው ሁኔታ አጣርተው መረጃ እንደሚሰጡን ተናግረዋል።
ክስተቱ በትናንትናው እለት አንድ ከአዲስ አበባ ወደ ዱባይ ሲበር የነበረ የበረራ ቁጥሩ EK724 የሆነ የኤምሬትስ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ መስመሩን ቀይሮ ወደ ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ሲጓዝ ፍላይ ራዳር ላይ ተመልክተናል (ምስሉ ላይ ይታያል)።
በተመሳሳይ በትናንትናው እለት በ ET227 የበረራ ቁጥር ያለው አውሮፕላን በትናንትናው እለት ከጅግጅጋ፣ እንዲሁም ET375 ከሀርጌሳ ወደ አዲስ አበባ ሲበሩ አቅጣጫ እንዲቀይሩ እንዳደረገ ተመልክተናል።
በአለም ዙርያ የሚከሰቱ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች ወደ አየር የሚለቋቸው ቅንጣቶች በተለያየ ግዜ በረራዎችን ከማስተጓጎል አልፈው እስከነጭራሹ ሲያሰርዙ ተስተውሏል።
የዛሬ 15 አመት ገደማ በአይስላንድ የተከሰተ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ 100,000 በረራዎችን አስተጓጉሎ የነበረ ሲሆን ይህም ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛው የአቪዬሽን መስተጓጎል ሆኖ ተመዝግቧል።