በአመራሮቹ መካከል እየተካረረ የመጣው ልዩነት በክልሉ እየታየ ያለውን የሰላም ጭላንጭል የሚያጨልም ነው” – ብጹህ አቡነ ማትያስ
በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል እየተካረረ የመጣው ልዩነት በክልሉ የተገኘችውን የሰላም ጭላጭል የሚያጨልም ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቀጻጻስ የሆኑት አቡነ ማትያስ ገልጸዋል፡፡
ብጹህነታቸው ይህን ያሉት ለህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል እና ለግዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በተናጠል በጻፉት ደብዳቤ ነው።
ፓትርያርኩ በደብዳቤያቸው ሁለቱን አመራሮች በአካል አግኝተው ለመወያየት ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካላቸው በመጠቆም ደብዳቤውን ለመጻፈ መገደዳቸውን አስታውቀዋል።
“በእልክ እኔ እሻላለሁ፣ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን፣ እኔ ብቻ ነኝ ለህዝብ የማስበው በሚል በተፈጠረው ውስብስብ ችግር የሚያዝን እንጂ የሚደሰት ህዝብ የለም” ሲሉ ጠቁመዋል።
“በአመራሩ መካከል የተፈጠረው መለያየት እንዳይበቃ በአንድነት ተስማምቶ ሲኖር በነበረው ህዝብ መካከልም ተጽእኖው እየወረደ ይገኛል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል::