በአቶ ልደቱ አያሌው ለመሠረት ሚድያ የተላከ
የፕሪቶሪያው ስምምነት በተፈረመ ማግስት “የፕሪቶሪያው ስምምነት ያሳዝናል፣ ያስደስታል፣ ያሳስባል!” በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ አስነብቤ ነበር። “ያሳዝናል” ያልሁት- ጦርነቱ ለጊዜውም ቢሆን እንዲህ በሰላማዊ ድርድር ሊቋጭ በሚሊዬን የሚገመቱ ወገኖቻችንን ህይዎት ባልተገባ የዕርስ-በርስ ጦርነት ማጣታችን እጅግ አሳዛኝ ስለነበር ነው።
“ማናችሁም በዘላቂነት ላታሸንፉ በቀላሉ የማይዎጣበት ጦርነት ውስጥ አታስገቡን” የሚለውን የአንዳንዶቻችንን ምክር “ጀሮ-ዳባ ልበስ” ብለው ወደዚያ ህዝብ ጨራሽና አውዳሚ ጦርነት ያስገቡን ግብዞች ከዚያ ሁሉ ዕልቂትና ውድመት በኋላ የተደረሰበትን ያን የፕሪቶሪያ ስምምነት እንደ ልዩ ስኬትና ድል ቆጥረው እንደ ሰላም አርበኛ ለመመስገንና ለመወደስ ሲፈልጉ እንደማየት ልብ የሚሰብር ክስተት አልነበረም።
“ያስደስታል” ያልሁት- ለጊዜውም ቢሆን የሰላም ስምምነት መፈረም በመቻሉና የህዝብ ዕልቂት በመቆሙ ነበር። የወደፊት ውጤቱ ምንም ይሁን ምንም ያ ህዝብ ጨራሽና አውዳሚ የሆነው ጦርነት ሲቆምና ህዝቡ ለጊዜውም ቢሆን የሰላም አየር ሲተነፍስ እንደማየት በርግጥም የሚያስደስት ክስተት አልነበረም።
“ያሳስባል” ለማለት የተገደድኩት- ስምምነቱ ጦርነቱን በዘላቂነት የሚያስቆምና ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ የሚችል እንዳልሆነ አስቀድሞ ግልፅ ስለ ነበር ነው። በርግጥም ስምምነቱ በቂ ዝግጅትና ድርድር ያልተደረገበት፣ በውጫዊ ጫናና ግፊት እንጂ በራስ ልባዊ ፍላጐት ያልተፈረመ፣ ዘላቂ መፍትሄን ለማምጣት ሳይሆን ለሌላ ዙር ጦርነት ጊዜ ለመግዛት ታስቦ የተካሄድ፣ ለጦርነቱ ምክኒያት የሆኑትን ቅራኔዎች በቅጡ ያላገናዘበና ዘላቂ መፍትሄዎችን በአግባቡ ያልዋጀ ስምምነት ስለነበር መሬት ላይ በተግባር ሊፈፀም እንደማይችል አስቀድሞ የታወቀ ነበር።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሆኖታል። ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመለወጥ የስምምነቱ ተፈራራሚና ባለቤት በሆኑት በፌደራል መንግስቱና በህወሓት ምክክር ተቋቋመ የተባለው ጊዜያዊ መስተዳድር አንዳችም ትርጉም ያለው ተግባር ሳይፈፅም የስራ ጊዜውን ጨርሶ ፈርሷል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዘደንት የነበሩትና በውስጠ-ድርጅታዊ ትግል ተሸናፊ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳም ያለ ተጨባጭ የስራ ውጤት ሊከርሙበት ፈልገው የነበረውን ስልጣን ወደው ሳይሆን ተገደው አጥተውታል።
ስለ ፕሪቶሪያው ስምምነት ውጤታማ አለመሆን ሁለቱ ተፈራራሚ ወገኖች አንዳቸው ሌላቸውን ተጠያቂ ለማድረግ ሲሞክሩ እያየን ነው። በህወሓት ውክልናና አባልነታቸው ምክኒያት ፕሬዘደንት ለመሆን የበቁት አቶ ጌታቸው ረዳ ለፕሪቶሪያው ስምምነት አለመፈፀም ተጠያቂነቱን ወደ ህወሀት በመግፋታቸው ለብልፅግናው አገዛዝ “ሰርግና ምላሽ” ሆኖለታል።
እንዲህ አይነቱ መካሰስ ራስን ያለ አግባብ ከተጠያቂነት ለማዳን የሚደረግ ሙከራ ካልሆነ በስተቀር ለስምምነቱ አለመተግበር ፌደራል መንግስቱ፣ ህወሓት ወይም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በተለየ ሁኔታ ወይም በተናጠል ተጠያቂ የሚሆኑበት ምክኒያት የለም። ራሳቸውን ካልዋሹ በስተቀር ሁሉም በውስጣቸው እንደሚያውቁት ስምምነቱ ገና ከጅምሩ በተግባር እንደማይፈፀም እየታዎቀ ለጊዜ መግዣነት ተብሎ የተፈረመ የታይታ ስምምነት ነበር።
በአጭሩ ጦርነቱን ያስቆመው በዋናነት የራሱ የጦርነቱ አስቀያሚ ገፅታ እንደሆነው ሁሉ፣ ስምምነቱን ፈራሽ ያደረገውም የችግሩን ምንጭ በአግባቡ መመርመር ያልሞከረውና ዛላቂውን መፍትሄ ለማስቀመጥ የተሳነው የራሱ የፕሪቶሪያው ስምምነት ደካማ ይዘት ነው።
የስምምነቱ ተፈፃሚ አለመሆን ከሴራ ፖለቲካ ጋር የተያያዘና አስቀድሞ የሚጠበቅ አይቀሬ ውጤት እንጅ ከአቅም ጋር የተያያዘ የማንም የአፈፃፀም ድክመት አይደለም።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ሰሞኑን አዲስ አበባ ላይ ጀነራል ታደሰ ወረደ ፈረሙት በተባለው የ“ቃል-ኪዳን” ሰነድ ግባተ-መሬቱ ተፈፅሟል። የ“ቃል-ኪዳን” ሰነዱ የተፈረመው በፕሪቶሪያው ስምምነት ፈራሚ ወገኖች ማለትም በፌደራሉ መንግስትና በህወሓት መካከል አይደለም። የፕሪቶሪያው ስምምነት ፈራሚ የሆኑት ሁለቱም አካላት በ“ቃል-ኪዳን” ሰነዱ ላይ ፊርማቸውን አላስቀመጡም። እንዲያውም አንዱ የፕሪቶሪያው ስምምነት ባለቤት የሆነው ህወሓት እንኳንስ ስምምነቱን ሊፈርም ሊያጨበጭብም በስነ-ስርዓቱ ላይ አልተገኘም።
አለመገኘትም ብቻ ሳይሆን አምስት ሰዎች ንግግር ባደረጉበት በዚህ የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ የህወሓት ስም አንድም ቦታ ላይ እንዳይጠቀስ ተደርጓል። ህወሓት ይህንን የ“ቃል-ኪዳን” ሰነድ እንኳንስ ሊያከብረውና ሊፈፅመው “አውቀዋለሁ”ም ሊለው የሚችል አይመስለኝም። የጀነራል ታደሰ ወረደ የወቅቱ ሹመትም ሆነ የ“ቃል-ኪዳን” ሰነዱ ከፕሪቶሪያው ስምምነት የመነጨ፣ ወይም የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚያድስና የሚያስቀጥል አይደለም። ይልቁንም ሰነዱ ከሀገሪቱ መደበኛ የህግ አሰራር የመነጨ ስለ መሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢ-ሜይል ፕሬዘደንት ለማስመረጥ ካደረጉት የታይታ ሙከራ ጀምሮ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር በግልፅ ታይቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የዶ/ር ጌዲዮን ንግግርም የበለጠ የሚያረጋግጠው ይህንኑ ዕውነታ ነው። ከዚያም በተጨማሪ የ“ቃል-ኪዳን” ሰነዱ የፊርማ ስነ-ስርዓት አጠቃላይ አካሄድ የፕሪቶሪያው ስምምነት የተፈፃሚነት ዘመኑ አልፎ የፌደራሉ መንግስትና የትግራይ ክልል ግንኙነት ከእንግዲህ ወደ ቅድመ-ፕሪቶሪያ ነባራዊ ሁኔታ /Statuesque anti/ መመለሱን በማያሻማ ሁኔታ አሳይቷል። በአጠቃላይ- የ“ቃል-ኪዳን” ሰነዱ የፕሪቶሪያው ስምምነት በተናጠል /Unilateral/ ውሳኔ መፍረሱን በይፋ ያረዳን ሰነድ ነው።
ሰነዱም የሁለት ወገን የስምምነት ውጤት ሳይሆን ፌደራል መንግስቱ በመደበኛ አሰራር ጊዜያዊ የክልል ፕሬዘደንት አድርጐ ለሾማቸው ለጀነራል ታደሰ ወረደ የሰጠው የስራ ኃላፊነት ማብራሪያ ሰነድ /TOR/ ነው። ጀነራል ታደሰ “ቃል-ኪዳን” የገቡት ለፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈፃሚነትና ለስምምነቱ ፈራሚ አካላት ሳይሆን ሹመቱን ለሰጧቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ነው።
የጀነራል ታደሰ አቋምና አካሄድ ምን ሊሆን እንደሚችል ወደፊት አብረን የምናየው ቢሆንም ከህጋዊ አሰራር አኳያ ግን የወቅቱ የጀነራል ታደሰ ሹመት በብዙ ዲፕሎማቶች ታጅቦ ከመፈፀሙ በስተቀር ከእነ አቶ አረጋ ከበደ ሹመት የተለየ ትርጉም የለውም። እንደ ፕሪቶሪያው ስምምነት ሁሉ በዚህ ሰነድ ላይ የተዘረዘሩት የስራ ኃላፊነቶችም መሬት ላይ ተፈፃሚ እንደማይሆኑ አስቀድሞ የታወቀ ነው። ህወሓት የማያውቀውና ያላመነበት ሰነድ በአሁኑ ወቅት ትግራይ ላይ ሊፈፀም እንደማይችል ከማናችንም በላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንቅቀው ያውቁታል።
ከአቶ ጌታቸው ረዳ በላይ የጀነራል ታደሰ ልብ በብዙ ርቀት ለህወሓት ሊያደላ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊገነዘቡ እንደሚችሉ መገመትም ከባድ አይመስለኝም። ይህ ሁሉ የሚያመላክተን የ“ቃል-ኪዳን” ሰነዱ የፊርማ ስነ-ስርዓት ድምቀት የበዛበት እንዲሆን የመደረጉ ሚስጥር በአደባባይ እየተነገረን ካለው ትርክት በተለየ “ውስጠ-ወይራ” ትርጉምና ይዘት ያለው ስለመሆኑ ነው። የፌደራል መንግስቱም ሆነ ህወሓት የፕሪቶሪያው ስምምነት “ሆድ ሲያውቅ ደሮ ማታ” እንዲሉ መሬት ላይ ተፈፃሚ እንደማይሆን አስቀድመው ያውቃሉና ስምምነቱ መፍረሱን በይፋ ሊነግሩን አልደፈሩም።
ያ- ዓለም ያደነቀውና ተስፋ የጣለበት የሰላም ስምምነት “እንዴት ይፈርሳል!?” በማለት ፈራሚዎቹ ለማስመሰልም ያህል እንኳን ሊደነግጡ ሲሞክሩም አልታየም። ሀቁን ቢናገሩ ሊያስከትል የሚችለው የዲፕሎማሲ ጫና ስላስፈራቸው እንጅ የፕሪቶሪያውን ስምምነት መፍረስ ሁለቱም ወገኖች የጠሉት አይመስልም። የሚገርመው የስምምነቱ አፈራራሚ የነበሩት የውጭ አካላት ዘላቂ ሰላም ያመጣል ብለው ተስፋ የጣሉበት የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲህ በአደባባይ መፍረሱን እያዩም ከመደንገጥ ይልቅ አዲስና ሌላ ተስፋ ሰጭ ስምምነት የተፈረመ አስመስለው ደስታቸውን ሊገልፁ ሲሞክሩ መታየታቸው ነው።
በአጭሩ- የሰሞኑ የሸራተን ሆቴል የፊርማ ስነ-ስርዓት በአንድ ወገን የተናጠል ውሳኔ የፕሪቶሪያው ስምምነት እስከወዲያኛው የፈረሰ መሆኑን በቀጥታም ባይሆን በደምሳሳው የተገለፀበት፣ ስነ-ስርዓቱም በአንፃራዊነት የሰፈነውን የትግራይ ሰላም ለማፅናት ተብሎ በቅንነት የተካሄደ ሳይሆን ለሌላ ዙር የጦርነት ዝግጅት የተካሄደ ስልታዊ የፕሮፓጋንዳና የዲፕሎማሲ ተውኔት እንደሆነ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት “ጦርነቱን ለጊዜው ማስቆም እስከተቻለ ድረስ የተጠየቀውን ሁሉ ዝም ብለን እንቀበል” ተብሎ እንደተፈረመው ሁሉ፣ የአሁኑ የ“ቃል-ኪዳን” ሰነድም “የተጠየቀው ሁሉ ይፈረምና ጊዜያዊ መንግስቱን በእጃችን እናስገባ” ተብሎ የተፈረመ ይመስላል። እንዲህ ዓይነቱ የዘ-ፈቀደ ስምምነት ጊዜ ከመግዛት ያለፈ ሌላ ዓላማና ትርጉም የለውም። እንደተለመደው የድብብቆሽ ጨዋታ ነው።
በእኔ ዕይታ አዲሱ ተሿሚ ጀነራል ታደሰ የፈረሙትን የ“ቃል-ኪዳን” ሰነድ በተግባር ሊያውሉት እንደማይችሉ ከሁላችንም በላይ ራሳቸው የሚረዱት ይመስለኛል። ጀነራል ታደሰ በተሰጣቸው ሹመትና በመጭው የስራ ዘመናቸው ታማኝነታቸው ለፌደራል መንግስቱም ይሁን ለህወሓት፣ ከዚያም በተለየ ገለልተኛ ሆነው ለመስራት ቢሞክሩ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የማስቀጠልም ሆነ የማስፈፀም አቅም ብቻ ሳይሆን ፍላጐትም የሚኖራቸው አይመስለኝም።
ጀነራል ታደሰ የተቀበሉት ሹመት የተፈጠረውን የፕሬዘደንትነት የኃላፊነት ቦታ ክፍተት ከመሙላት ባለፈ ሌላ ትርጉም ያለው ለውጥ የማምጣት ሚና አይኖረውም። ጀነራሉ ልባቸው ከህወሓት ጋር ከሆነ ሹመቱ በርግጥም ተመኝተው ያገኙት ዕድል ስለሚሆን ፌደራል መንግስቱን የበለጠ ለመጋፈጥ ጥቅም ላይ ይውላል። ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ወግነው ወይም ገለልተኛ ሆነው ለመስራት አስበው ከሆነም ሹመቱ በጫንቃቸው ላይ የተጣለ ዕዳ ስለሚሆን የአቶ ጌታቸውን ዕጣ-ፈንታ ከመቀበል የተለየ ሚና ሊኖራቸው አይችልም።
ሌላ አዲስና ሀቀኛ ስምምነት ውስጥ እስካልተገባ ድረስ በኔ ዕይታ ዕድሉም-ዕዳውም ከእንግዲህ የሚያመራው ወደ ሰላም ሳይሆን ወደ ሌላ ዙርና የበለጠ አውዳሚ ወደ ሆነ ጦርነት ነው። ከዚህ ባለፈ- የ“ቃል-ኪዳን” ሰነዱ ሰላምን ለማፅናት ታስቦ የተፈረመ የችግር-መፍቻ ሰነድ አይደለም። ሁለቱ ፈራሚ አካላት ጦርነትን ዋና የዓላማቸው ማስፈፀሚያ ስልት አድርገው ማየትን እስከቀጠሉበት ድረስ፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓት ከምድረ-ገፅ ካልጠፋ ስልጣኔ አይፀናም ብለው መጨነቃቸውን ካላቆሙ በስተቀር መቸም ቢሆን በመካከላቸው ለተፈፃሚነት የሚበቃ ሀቀኛ ስምምነት መፈራረም አይችሉም።
“ልባቸው” ተከፍቶ ቢታይ አንዳቸው ሌላቸውን በኃይል አሸንፈው፣ ሲቻልም አጥፍተው ነው እንጅ እውቅና ተሰጣጥተውና ተቻችለው የመኖር ፍላጐት ፈፅሞ የላቸውም። ዛሬም ውስጥ-ውስጡን እየተብላላ የሚገኘውን ሌላ ዙር ጦርነት ከመፈንዳት ማስቀረት የሚቻለው የፕሪቶሪያውን ስምምነት በማስቀጠልም ሆነ በተናጠል በማፍረስ አይደለም። መፍትሄው በአንድ በኩል የፕሪቶሪያው ስምምነትም ሆነ የሰሞኑ የ“ቃል-ኪዳን” ሰነድ የችግሩን ምንጭ በአግባቡ ያልተገነዘበና ጦርነቱንም በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችል መፍትሄ ያልቀመረ መሆኑን አምኖ በመቀበል ነው። በሌላ በኩልም መቸውንም ጊዜ ቢሆን በጦርነት የሚገኝ ዘላቂ ድልና ውጤት እንደሌለ ከልብ በማመን የፌደራል መንግስቱና ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚተካ ሌላ አዲስና ሀቀኛ ስምምነት መፈራረም ሲችሉ ነው።
ከማንኛውም ክልል ጋር የሚካሄድ ድርድርም ሀገር-ዓቀፋዊ ከሆነ መዋቅራዊ መፍትሄ ጋር ተሳስሮ ካልተፈፀመ በስተቀር በተናጠል ድርድር ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ ሊያስገኝ አይችልም።
የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነው የኢትዮዽያ ህዝብም ሆነ ጦርነትን ማስቀረት የሚፈልጉ የውጭ መንግስታትና ተቋማት የፕሪቶሪያውን ስምምነት መክሸፍ ተከትሎ በተለዬ የኃይል አሰላለፍ የበለጠ ህዝብ ጨራሽ ጦርነት ከፊታችን አፍጥጦ እየመጣ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። አደጋውን በመገንዘብ ሌላ አዲስና ሀቀኛ የሰላም ስምምነት በአስቸኳይ እንዲፈረም የሚያስችል ጫና በሁሉም ኃይሎች ላይ መፍጠር ካልተቻለ ግን ከፊታችን አፍጥጦ እየመጣ ያለውን ሌላ ዙር አውዳሚ ጦርነት በቀላሉ ማስቀረት አይቻልም።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ለጊዜው የፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም አስጠብቆ የማስቀጠል ዕድል ከእንግዲህ የለውም። አዲሱ የአዲስ አበባ የ“ቃል-ኪዳን”ሰነድም ተራ የፕሮፓጋንዳና የዲፕሎማሲ ተውኔት እንጅ ሀቀኛ የሰላም አጀንዳ አይደለም።
ሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንድታገኝ፣ አግኝታም ከህልውና ጥፋት እንድትድን ከተፈለገ ታይታና ሸፍጥን ማቆምና ለሀቀኛ ውይይትና ድርድር መገዛት የግድ ይለናል። አለበለዚያ የወደድነው ጦርነት በልቶ ይጨርሰናል።
ልደቱ አያሌው ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም
@MeseretMedia