የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፣ የክልሉ ጸጥታ ሃላፊና የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ጀኔራል ታደሠ ወረደ ተሠጥተዋቸው የነበሩትን የሥራ ዝርዝሮች መፈጸም አልቻሉም ነበር በማለት ከቢቢሲ ፎከስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተችተዋል።
የጀኔራል ታደሠ የሥራ ዝርዝር በውድቀት የተሞላ ነበር ያሉት ጌታቸው፣ እርሳቸውን በወቅቱ ከሃላፊነት ማንሳት አለመቻላቸው ውድቀታቸው እንደኾነ ገልጸዋል። ሥልጣኑን ጠቅልሎ ለመያዝ ከሚፈልገው ደብረጺዮን ከሚመሩት የሕወሓት አንጃ የሚመጣው ከቁጥጥር ውጪ የኾነ የሥልጣን ጥማት፣ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት ተግዳሮት ኾኖ ሊቀጥል እንደሚችልም ጌታቸው ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ ሥልጣን ከሚጎመዡት የሕወሓት ሰዎች ሁሉ የተሻሉት ጀኔራል ታደሠ ናቸው በማለት ሊያሳምኗቸው እንደሞከሩና የታደሠ ሹመት የጠቅላይ ሚንስትሩ ውሳኔ እንደኾነ ጠቅሰዋል።
የትግራይን ፖለቲካ ይበልጥ አስቸጋሪ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል፣ በመንግሥት ሥር መኾን የነበረበት ሠራዊት እስካኹን ራሱን የቻለ አካል አድርጎ መቆጠሩ ተጠቃሽ እንደኾነም ጌታቸው አውስተዋል። ኤርትራን በተመለከተ፣ በእሳቸው አስተዳደር ውስጥ የተወሰኑ ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለመገናኘት ሲሞክሩ እንደነበር ጌታቸው ተናግረዋል።