መንግሥት በኦሮሚያ ክልል በክላስተር ከተዘራው የስንዴ ምርት 70 በመቶውን ከአርሶ አደሮች በወቅታዊ የገበያ ዋጋ ገዝቶ እየወሰደ መኾኑን ታውቋል።
ባኹኑ ወቅት አንድ ኩንታል ነጭ ስንዴ በገበያ ላይ 5 ሺሕ 500 ብር እየተሸጠ ሲኾን፣ አርሶ አደሮች ግን በማዳበሪያ ዋጋ ውድነት የተነሳ ዋጋው አትራፊ እንዳልኾነ ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች፣ የምርታቸውን 70 በመቶ ለመንግሥት ለመሸጥ የገቡት ስምምነት ባይኖርም፣ የበላይ አካል ትዕዛዝ ነው በሚል እንዲሸጡ እየተገደዱ መኾኑን ገልጸዋል።
ኾኖም ይህ አሠራር በክልሉ ወጥ በኾነ ኹኔታ እየተተገበረ አይደለም ተብሏል። የስንዴ ግዥውን ትዕዛዝ የሚያስፈጽሙት፣ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ መዋቅሮች እንደኾኑ ተሰምቷል።