መንግስት የመከላከያ የክብር አባል ያደረገውን የአክቲቪስት ስዩም ተሾመን አድራሻው አላውቅም ሲል ዛሬ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለፀ።

ግለሰቡ በእስር ላይ የሚገኙትንና ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ ያሉት አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና አቶ ክርስቲያን ታደለን ስማቸውን በመጥቀስ “ታጥቀው መንግስት እንገለብጣለን ብለዋል” በማለት በፍርድ ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር በችሎት መድፈር ተከሷል።
በዚህም መሰረት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስዩም ተሾመ መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም እንዲቀርብ ትዕዛዝ ቢሰጥም ሳይገኝ ቀርቷል።
ተከሳሹን ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ የታዘዘው የፌዴራል ፖሊስ የመንግሥት ተንታኝና የመከላከያ የክብር አባል የሆነው ስዩም ተሾመን አድራሻውን አላውቀውም በማለት ሳያቀርበው ቀርቷል።
በችሎቱ የቀረቡት አቶ ዮሐንስ ቧያለው “ይህንን ግለሰብ ከአሁን ቀደምም በስም ማጥፋት ወንጀል ከስሼው በፍርድ ቤት ተቀጥቷል። ቋሚ አድራሻ ቢኖረውም ፖሊስ በተደጋጋሚ ሄዶ እያየ ሰላምታ እየሰጠው ነው የሚመለሰው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ተከሳሹ ያኔ የተቀጣው ቅጣት ባለፈጸሙና ትምህርት ባለማግኘቱ አሁንም ተመሳሳይ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል።
አቶ ስዩም ተሾመ መንግስት ቤት የሰጠው፣ ደሞዝ የሚከፍለው እና ተሽከርካሪ እና ጥበቃ የመደበለት የመንግሥት አክቲቪስት እንደሆነ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ “አማራ ቢሆን ኖሮ ፖሊስም ሆነ አቃቤ ሕግ ከየትም ፈልገው አንጠልጥለው ያመጡት ነበር” ብለዋል።
ሌላው ከሳሽ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው የፌዴራል ፖሊስ አድራሻውን አላውቀውም ማለት “ወስፌ ሲለግም ቂቤ አይወጋም” የሚለውን አባባል እውነተኝነት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
አቶ ክርስቲያን “እኔን አጅባችሁ ውሰዱኝና ቤቱን ላሳያችሁ። የመንግስት ሹመኛን የሚጠብቀው የፌደራል ፖሊስ አካል እኛን የሕዝብ እንደራሴዎችን ከቤተሰባችን ፊት ደብድቦና አዋርዶ ለማምጣት ያልተቸገረው ፌዴራል ፖሊስ፣ ላገኛቸው አልቻልኩም ማለቱ ስላቅ ነው” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
አቶ ዮሐንስ ስዩም ሲከሰስ የማይቀርበውና ከለላ የሚሰጠው “በመንግሥት ደረጃ የአማሮች ስም እንዲጠፋ ስለተፈለገ ነው” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም አክቲቪስት ስዩም ተሾመ ሰኔ 6 ቀን 2014 ዓ.ም ከባድ የስም ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም በአቶ ዮሐንስ ቧያለው ክስ ተመስርቶበት ነበር። በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንፋስ ስልክ ላፍቶ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 56905 ስዩም ተሾመ የአቶ ዮሃንስ ቧያለውን ስም በማጥፋቱ የአራት ወር እስራት እና የ100 ሺ ብር ቅጣት አስተላልፎበት ነበር።
ምንም እንኳን ፍርድ ቤቱ ቅጣት ቢወስንም ግለሰቡ እንዳይቀጣ በገዢው መንግሥት ከለላ ተደርጎለታል የተባለ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ “የትኛውም ፍርድ ቤትና ፖሊስ እኔን መያዝ አይችልም” ሲል በሚዲያ መናገሩ ይታወሳል።
የፀጥታ ኃይሉም ወንጀለኛውን ለሕግ አቅርቦ ፍርዱ እንዲፈጸም ሳያደርግ ቀርቶ አሁንም ግለሰቡ ተመሳሳይ ጥፋት እየፈጸመ እንደሚገኝ ታውቋል።
ፍርድ ቤቱም በድጋሚ የፌደራል ፖሊስ ስዩም ተሾመን እንዲያቀርባቸው ለሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ/ም ቀጠሮ ሰጥቷል።