ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሆነው ስልጣን ተረከቡ።

ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሆነው ስልጣን ተረከቡ። ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምን አሉ ?

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፥ ” ባለፈው አንድ ወር ገደማ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት፣ የፕሪቶርያን ስምምነት እና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ምክር በማከል ሰፊ ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል ” ብለዋል።

” የአቶ ጌታቸው ረዳ የሥልጣን ዘመን በሕጉ መሠረት ሲያበቃ የሚቀሩ ቁልፍ ሥራዎችን የሚያከናውን አካል፣ ግዝያዊ መንግሥቱ መቀጠለ አለበት የሚል ድምዳሜ ከተያዘ በኋላ፣ ይሄንን ሽግግር ማን መርቶ ከግብ ሊያደርስ ይችላል ? የሚሉ ውይይቶችን ስናደርግ ቆይተናል ” ሲሉ ገልጸዋል።

ዛሬ በይፋ እና በሰላማዊ መንገድ በአዲስ ባህል የሥልጣን ሽግግሩን እና ቅብብሎሹን ለማካሄድ የተዘጋጀ ፕሮግራም መካሄዱን አሳውቀዋል።

” ጄኔራል ታደሰ ባለፋት ሁለት ዓመታት የአቶ ጌታቸው ምክትል ሆነው ያገለገሉ ሰው ናችው ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ” ባለፋት ሁለት ዓመታት የነበሩ ድካሞችን እና ጥንካሬዎችን በግልጽ የሚገነዘቡ ሰው ናቸው ” ብለዋቸዋል።

” አሁን ትግራይ ውስጥ ያለውን ክፍተት ሞልተው ወደ ፊት ሊወስዱ ይችላሉ የሚል እምነት በብዙ አካላት የታመነ ነው። የትግራይ ሕዝብ የጠማውን ሰላም እና ልማት፣ እንደ ሌሎች ወንድሞቹ ወጥቶ የመግባት መሻት ስናሳካ፣ ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም እጅግ ጠቃሚ የሆነ ነገር ሠርቶ ለማለፍ ታሪክ የሰጣቸውን ዕድል እንደሚጠቀሙበት ተስፋ አደርጋለሁ ” ብለዋል። ጄኔራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንትነትን ሲረከቡ የፈረሙት ” የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የተልዕኮ አፈጻጸም የቃል ኪዳን ሰነድ ” ምን ይላል ?

  1. የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሂደት፣ በጅምር ያለው እንዲጠናቀቅ እና በቀሪ አካባቢዎችም በፍጥነት እንዲተገበር ማድረግ፤
  2. በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ትጥቅ የመፍታት እና የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ተግባር በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ ማድረግ፤
  3. በክልሉ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ፤ ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለሰላም እና ለጸጥታ ጠንቅ የሆኑ ጉልህ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ፤ ለዚህም ተገቢውን የቁጥጥር እና የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት፤
  4. መደበኛ የልማት ሥራዎች፣ መንግሥታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ እንዲሁም የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንዲሣለጡ ማድረግ፤
  5. ከሕገ መንግሥታዊ እና ከሕጋዊ ሥርዓት፣ ከሀገር ሉዓላዊነት እና ከፕሪቶርያ ስምምነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ፤
  6. ክልሉ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ፤ በክልሉ የሲቪክ እና የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ የሆኑበት፣ የፖለቲካ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ደሞክራሲያዊ ዐውድ እንዲፈጠር መሥራት፤
  7. የክልሉ ሕዝብ፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ተዋንያን በሀገራዊየምክክር ሂደት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤
  8. የክልሉ መንግሥታዊ የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ሕዝቦች ትሥሥር እና መልካም ግንኙነት የሚያጠናከሩ፣ ሕግ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚያስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ፤

ጄነራል ታደሰ ወረደ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት በመሆን ሥራቸውን ሲጀምሩ ከላይ የተዘረዘሩትን ኃላፊነቶችን በትጋት እና በታማኝነት ለመወጣት ቃል ገብተው ፈርመዋል።