ፈላሻው በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ከአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ተገደው ተባረሩ

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ቤተ እስራኤላዊው አብርሃም ንጉሴ ዛሬ አፍሪካ ኅብረት የሩዋንዳውን የዘር ጭፍጨፋ ለማሰብ ካዘጋጀው ስብሰባ ተገደው እንዲወጡ ተደርገዋል።

አምባሳደር ከስብሰባው እንዲወጡ የተገደዱት፣ እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማዊያን ላይ የምትፈጽመውን መጠነ ሰፊ ጥቃት የሚቃወሙ በርካታ አባል አገራት አምባሳደሩ በተገኙበት ስብሰባ ላይ አንካፈልም ብለው ተቃውሞ በማሰማታቸውን እንደሆነ ተገልጧል። የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ አምባሳደሩ ከስብሰባው ተገደው መውጣታቸውን ተከትሎ በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃሙድ የሱፍን መውቀሱን የእስራኤል ጋዜጦች ዘግበዋል።

ሚንስቴሩ፣ ድርጊቱ የዘር ጭፍጨፋ የደረሰባቸውን የሩዋንዳ ቱትሲዎች መታሰቢያ ክብር ያልሰጠ፣ ተቀባይነት የሌለውና፣ የሩዋንዳና አይሁድ ሕዝቦችን ታሪክ ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው በማለት መተቸቱን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። እስራኤል በድርጊቱ አሳሳቢነት ዙሪያ በዲፕሎማሲያዊ መስመሮች እንደምትገልጽ ጠቁማለች ተብሏል። አብርሃም የእስራኤል አምባሳደር ሆነው የተሾሙት፣ ባለፈው ዓመት ነሃሴ ነበር።