ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ ሕወሓት ከስልጣን አሰናብቶ ከመቀሌ ዱባይ ያባረራቸውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳን ከሃላፊነት ማሰናበታቸውን ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው በትግርኛ ቋንቋ ባስላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል።

ዐቢይ፣ ጌታቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት በመኾን ያበረከቱትን አስተዋጽዖ ፌዴራል መንግሥቱ እውቅና እንደሚሠጠው በመግለጽ ጌታቸውን አመሰግነዋል።
በሁለት አመቱ የትግራይ ጦርነት አብይን ሲሳለቁባቸው የነበሩት ጌታቸው፣ በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደሩን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚንስትሩ የተሾሙት ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር።
ዐቢይ፣ የቆይታ ጊዜው ለተጠናቀቀው ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ዕጩ ፕሬዝዳንቶችን የትግራይ ሕዝብ ለጽሕፈት ቤታቸው እንዲጠቁም ከቀናት በፊት ጥሪ ማድረጋቸው አይዘነጋም። ኾኖም ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመሩት የሕወሓት ክንፍ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ በተናጥል ፕሬዝዳንት ለመሾም እየሞከሩ ነው በማለት ጥሪውን ውድቅ አድርጎታል። ሕወሓት ጌታቸው ረዳን እንዳሰናበተ ከገለፀ ቆይቷል።