እገታው ግድያው ቀጥሏል ! የሟች ቤተሰቦች አስክሬን ለማምጣት ሄደዋል …. ከእገታው በኃላ የታጋች ቤተሰቦች በሚሊዮን ብር እየተጠየቁ ነው።

“ የሟች ቤተሰቦች አስክሬን ለማምጣት ሄደዋል ” – የአንዱ ሟች ቤተሰብ

ትላንት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ “ጎሃ ፅዮን” እና “ቱሉ ሚልኪ” መካከል ታጣቂዎች አንድ ሙሉ ተሽከርካሪ ተሳፋሪዎችን መገታቸው ከዛም ውስጥ የተገደሉ መኖራቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

አንድ የሟች የቅርብ ቤተሰብ  ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፣ አንድ የልጆች አባት እንደተገደሉ፣ ነገ የቀብር ሥርዓታቸው ይፈጸማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ “ የሟች ቤተሰብ አስከሬን ለማምጣት ሄደዋል ” ብለዋል።

ሌላኛው የሌላ ሟች ጓደኛ በበኩላቸው፣ ሹፌሩን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተሳፋሪዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ፣ የሟቾቹን አስክሬን ወደ ትውልድ ቦታቸው ለማምጣት የሟች ቤተሰቦች ዛሬ ወደ እገታ ቦታው እንደሄዱ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

የሟቾች ወላጆች የሟቾቹን አስክሬን ገና ሊቀበሉ በመሆኑ፣ ሀዘናቸውም ስለበረታ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት የሚያስችል መረጋጋት ላይ አለመሆናቸው ተመልክቷል።

የሹፌሮችን ውሎ የሚከታተለው ጣና የአሽከርካሪዎች ማኀበር በበኩሉ፣ በታጣቂዎች ታገቱ ከተባሉት ተሳፋሪዎች መካከል በርካቶች በጥይት ተመትተው መገደላቸውን ከስፍራው መረጃ እንደደረሰው  ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

ከተገዱሉት ተሳፋሪዎች ባሻገር ታፍነው የተወሰዱ እንዳሉም ያመለከተ ሲሆን፣ እገታው የተጸመው ትላንት (ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2027 ዓ/ም) መሆኑን ተናግሯል።

ስለእገታው ከመንግስት እስካሁን በግልጽ የተባለ ነገር ባይኖርም፣ በእገታው ቦታ የፌደራል ፓሊስ ደርሶ እንደነበር በማኀበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ ተስተውሏል።

ስለጉዳዩ ማብራሪያ የጠየቅናቸው በኢትዮጵያ ፌደራል ፓሊስ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀይላን አብዲ፣ ስራ ላይ እንደሆኑ በመግለጻቸው ለጊዜው ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም። ምላሽ ከሰጡን የምናቀርብ ይሆናል።

የትላንቱ እገታ በተፈጸመበት አካባቢ ከ19 ቀናት በፊት ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ማርቆስ በርካታ ተሳፋሪዎች ይዞ ሲጓዝ የነበረ ” ፈለገ ግዮን ” ባስ ታጣቂዎች አስቁመውት ሙሉ ተሳፋሪዎች መታገታቸውን የአይን እማኝ ሹፌሮች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አሳውቀው ነበር።

ከእገታው በኃላ የታጋች ቤተሰቦች በሚሊዮን ብር እየተጠየቁ ነው።