በዛፍ ጥላ ስር የሚኖሩት ከ6 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች

በዛፍ ጥላ ስር የሚኖሩት ከ6 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች

(መሠረት ሚድያ)- ከስድስት ሺህ በላይ የሚሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ አጥተው በዛፍ ጥላ ስር ሕይወታቸውን እየገፉ እንደሚገኙ ለመሠረት ሚዲያ ተናገሩ። 

ከዛሬ ሶስት አመት በፊት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ አቅራቢያ ተጠልለው እንደሚገኙ የተናገሩት ተፈናቃዮቹ ቀደም ሲል በመንግስት ሲቀርብ የነበረው ወርሃዊ ድጋፍ መቋረጡን እና በመጠለያ ካምፑ ውስጥ ርሀብ መከሰቱን ተናግረዋል።

በመጠለያው ውስጥ ከሚኖረት አንዷ ወ/ሮ ሐሊማ ሙሄ ለመሠረት ሚዲያ እንዳረጋገጡት “ሕፃናትና እድሜያቸው ዘለግ ያሉ አረጋውያን በበሽታ ወድቀዋል። ሞተው አፈር ያለበስናቸውም አሉ። ከወለጋ ተፈናቅለን በዚህ ካምፕ ውስጥ የተጠለልነውን ሰዎች የፌደራሉም ሆነ የክልሉ  መንግስት እንደ ዜጋ አይመለከተንም፣ ምግብና መድሀኒት ከተቋረጠ ከአራት ወር በላይ አልፎታል። የሚላስ የሚቀመስ የለም” ሲሉ ነው የነገሩን።

“ካምፑ ለሌላ አገልግሎት ታቅዶ የተቋቋመ በመሆኑ ከወለጋ የመጣው ተፈናቃይ ብዛትና ካምፑ የመያዝ አቅሙ ባለመመጣጠኑ ምክንያት አብዛኛዎቻችን ውለን የምናድረው በአካባቢው ባለ ዛፍ ስር እና ቁጥቋጦ ተጠግተን ነው። ሕፃናት፣ እናቶች እና ሽማግሌዎች ሲኖሩበት የነበረው  ድንኳንም በእርጅና ምክንያት ተቀዳዶ አገልግሎት እየሰጠ ባለመሆኑ ሁላችንም ፀሀይ ላይ ተሰጥተናል” ሲሉ የነገሩን ደግሞ ከተፈናቃዮቹ አንዱ የሆኑት አቶ መሐመድ ይመር ናቸው።

ይህንኑ አስመልክቶ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ለማመልከት በየፅህፈት ቤቱ ደጅ ብንጠናም “በወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ስብሰባ ላይ ነን” በሚል ልናገኛቸው አልቻልንም ብለዋል ተፈናቃዮቹ ።

ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት በሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል በተለይ በደቡብ ወሎ ሐርቡ፣ ሐይቅ አቅራቢያ፣ መካነ ሰላም፣ መቅደላ ማሻ በሰሜን ወሎ ጃራ፣ በምስራቅ እና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች ተጠልለው ይገኛሉ።

እነዚህን ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው ለመመለስ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም “አሁንም ድረስ ቤትና ንብረታችን  በታጣቂዎች እጅ በመሆኑ ብንመለስ ጥቃት ይደርስብናል” በማለት ተፈናቃዮቹ ስጋታቸውን ገልፀዋል።