በጋምቤላና ደቡብ ሱዳን አዋሳኝ አካባቢዎች አዲስ ሰብዓዊ ቀውስ መከሠቱን ዓለማቀፉ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
በደቡብ ሱዳኗ የላይኛው ናይል ግዛት የመንግስት ወታደሮችና አንድ አማጺ ቡድን በቅርቡ መጋጨታቸውን ተከትሎ፣ ከየካቲት ሦስተኛ ሳምንት ጀምሮ በትንሹ 10 ሺሕ ስደተኞች ወደ ጋምቤላ ገብተዋል ተብሏል።
ስደተኞቹ ወደ ጋምቤላ ባጭር ጊዜ ውስጥ በብዛት መግባታቸው፣ በክልሉ የኮሌራ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ላይ ጫና እንደፈጠረ ድርጅቱ አውስቷል።
ያም ኾኖ ከጤና ሚንስቴር ጋር በመተባበር ከየካቲት መገባደጃ ጀምሮ ለ560 የኮሌራ ታማሚዎች ሕክምና መስጠቱን ድርጅቱ ጠቅሷል።
ጤና ሚንስቴር ባሁኑ ወቅት በክልሉ ዕድሜያቸው 1 ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆኑ 990 ሺሕ ያህል ሰዎች በአፍ በጠብታ የሚሰጠውን ክትባት ብመስጠት ላይ ነው።