ግለሰብ፣ ፓርቲ፣ መንግሥት እና አገር (በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ)

ግለሰብ፣ ፓርቲ፣ መንግሥት እና አገር (በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ)

አምባገነናዊ ስርዓቶች ግለሰብ፣ ፓርቲ፣ መንግሥት እና አገርን ለዜጎቻቸው እንደማይነጣጠሉ አስመስለው ያቀርባሉ። ግለሰቡን ከነካችሁ ፓርቲው ይፈርሳል፣ ፓርቲውን ከነካችሁ፣ መንግሥቱ ይፈርሳል፣ መንግሥቱን ከነካችሁ አገሩ ይፈርሳል። እውነት አላቸው። አምባገነኖች እና የአገዛዙ ጥቅመኞች ሕልውናቸውን ከአገሩ ሕልውና ጋር አስተሳስረው ነው የሚኖሩት። ኢሕአዴግ ከመውደቁ ትንሽ ሰሞን ቀደም ብሎ በአማርኛ ዝና ያገኘ አንድ የትግርኛ አባባል ነበር “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትትረፍ።” በግለሰቦች እና አገዛዞች መተሳሰር ምክንያት ዜጎች አምባገነኖችን ለመጣል ሲታገሉ አገራቸውንም ራሳቸው ላይ ይማፍረስ ስጋት አላቸው። ስለዚህ አምባገነኖችን መታገል በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ነገር ግን የማይቻል አይደለም።

የማይሻር ግለሰብ እና የማይቀየር የፖለቲካ ፓርቲ ያለበት መንግሥት መጨረሻው ለአገሩ ጠንቅ መሆን ነው። ግለሰቡም፣ ፓርቲውም ዘላቂ ዕድሜ የላቸውም። በመሆኑም ዜጎች መፃዒ ዕጣ ፈንታቸውን በሰቀቀን እንዲጠብቁ ይገደዳሉ። ተወደደም ተጠላም በብዙኃን ይሁንታ የሚወጣ እና የሚወርድ መንግሥት ያለበት አገር የተሻለ ተስፋና ሰላም ለሕዝቡ ይሰጣል። ነገር ግን በብዙኃን ይሁንታ መውጣት እና መውረድ ብቻ በቂ አይደለም። ገዢዎች በሥልጣን ላይ በሚቆዩበት ጊዜ ማድረግ የሚችሉት ነገር ካልተገደበ እያደር አውዳሚ ከመሆን አይመለሱም።

ይባስ ብሎ፣ በአምባገነናዊ ስርዓቶች ውስጥ ግን ሥልጣን ላይ መውጫ እና ሥልጣን ላይ መሰንበቻው መንገድ ነውጥ ብቻ ነው። ባለ ፍፁም ሥልጣኑ – አምባገነኑ – በወደቀ ቁጥር፣ ቢያንስ በየትውልዱ ትርምስ ይኖራል። አጥኚዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ ላለፉት ሁለት መቶ ዓመታት፣ ትልቅ ጦርነት ያላየ ትውልድ የለም የሚሉት ለዚህ ነው።

https://befeqe.blogspot.com/2025/03/—.html