ታግተው ጠፍተው የነበሩ 13 ተጠርጣሪዎች ከአራት አመት እስከ ስድስት ዓመት እስራት ተላለፈባቸው
(መሠረት ሚድያ)- በአማራ ክልል ተከስቶ ከነበረ የፀጥታ መደፍረስ ጋር በተገናኘ በሽብር ወንጀል የተከሰሱ 13 ተጠርጣሪዎች ከአራት አመት እስከ ስድስት ዓመት የሚደርስ እስራት በዛሬው እለት ተላልፎባቸዋል።

በዚህም መሰረት በእነ መላክ ምሳሌ መዝገብ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ለሁለት ዓመት ያህል በሕግ ቁጥጥር ስር ሆነው በፍርድ ቤት ሲከራከሩ የቆዩት 13 ተከሳሾች ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።
የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥት እና የሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ዛሬ ባስቻለው ችሎት ወጣት ዜና ኃይሉን በስድስ ዓመት፣ አንዱአለም አሻግሬ፣ ዓለም ሁሉ ጤናን እና ፍቃዱ መንግስቴን በአምስት ዓመት ከስድስት ወር ቀጥቷል።
አወቀ ስንሻውን፣ ማናዬ አየለን፣ አብርሐም መልካሙን እና ውበት አካል አራት ዓመት ከአስር ወር እንዲሁም ጌጤ አመኑ አራት ዓመት ከአምስት ወር ቀጥቷል።
በሌላ በኩል ኤርሚያስ መኩሪያ፣ መላክ ምሳሌ እና ይልማ በዛብህ በአራት ዓመት እስራት ሲቀጡ ወ/ሮ ቅድስት ከበደ በሁለት ዓመት ገደብ ከእስር እንድትፈታ ሲል ወስኗል።
በዛሬው ችሎት ውሳኔ የተሰጣቸው እስረኞች ከ2015 ዓ/ም ከሚያዚያ ወር መጨረሻ ጀምሮ እስከ ግንቦት ማብቂያ ድረስ የገቡበት ሳይታወቅ ቆይቷል።
ከአንድ ወር በኋላ የፌደራል ፖሊስ በገላን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈፅምባቸው መገኘቱም በወቅቱ አነጋጋሪ ዜና ሆኖ እንደነበር ይታወሳል።
በዚያን ወቅት ቅድስት ከበደ የተባለችው ተጠርጣሪ በምርመራ ላይ በደረሰባት ድብደባ ፅንስ ማስወረዷም ለብዙ ጊዜ ዜና ሆኖ ነበር።