የገነት አራጌ ስቃይና የብርሃኑ ነጋ ጭካኔ ! !
ምስሏን የምታዩት ወጣት ገነት አራጌ ትባላላች። የኢዜማ አባልና ከፍተኛ አመራርም ነበረች ። ኢዜማን ከተቀላቀሉ ብሩህ አይምሮ ከነበራቸው በርካታ ወጣት ሴቶች መሃከል አንዷ ነበረች። እንደሌሎቹም ወጣት ሴቶች በኢዜማ ላይ የነበራቸው ተስፋና ለኢዜማ የነበራቸው ፍቅር ገደብ አልነበረውም።

ዛሬ ከእነዚህ ወጣት ሴቶች መሃከል አንዳቸውም በኢዜማ ውስጥ የሉም። ከኢዜማ ጋር እንዲፋቱ ያደረጋቸው ዋናው ምክንያት፣ ኢዜማ ሁነኛ የተቃዋሚ ፖለቲካ ሚና በመጫወት የአብይ አህመድን ገደብ ያጡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የደህንነትና የውጭ ግንኙነት ቀውስ ጠማቂ እርምጃዎች በመቃወምና አገዛዙን ተጠያቂ ከማድረግ ፋንታ የብልጽግና ፓርቲ የቤት ውስጥ ባሪያ መሆኑ ነው።
በዚህ ላይ የአብይ አህመድ አገዛዝ ምንም አይነት ማስመሰያ ምክንያት ወይም ሰበብ ሳይኖረው፣ የአማራን ህዝብ ቅስም ለመስበር ያወጀው ጦርነት፣ አማራ የሆኑትን የኢዜማ ወጣቶች ያስቆጣና ድርጅቱን በገፍ ለቀው እነዲወጡ ያደረገ ነው። ገነት አራጌ ከእነዚህ ወጣቶች አንዷ ነች። በአማራ ህዝብ ላይ የመከራ ዶፍ ከሚያወርደው የአብይ አገዛዝ ጋር በአጋርነት ተጣብቆ የሚሰራውን የቀድሞ ድርጅቷን ትጠየፋለች።
ገነት፣ የአብይ አህመድን “ትጥቅና ቀበቶ እናስፈታለን” የሚል እብሪት ለማስተንፈስ መላው የአማራ ክልል ህዝብ “ሆ” ብሎ በተነሳበት ወቅት ባህርዳር ነበረች። በዛ ወቅት፣ በደርግ ዘመን ይደረግ እንደነበረው የቀይ ሽብር እርምጃ፣ የአብይ አህመደ ጭራቅ ወታደሮች፣ የባህር ዳር ወጣቶችን፣ በለሌት ከየቤታቸው እየጎተቱ እያወጡ፣ በደጃፋቸውና በወላጆቻቸው ፊት በጭካኔ ሲረሸኑ በአይኗ አይታለች ።
ይህን የአይን ምስከርነቷን ለኢዜማ አመራሮች፣ ለብርሃኑ ነጋ ተናግራለች። ብርሃኑ ነጋ በቀይ ሽብር ዘመን፣ ህይወቷ የጠፋ ብሩህ አይምሮ የነበራት፣ ከመለስ ዜናዊ ጋር የህክምና ትምህርቷን ስትከታተል የነበረች፣ እህት እንደነበረቸው ስለምታውቅ፣ አብይ አህመድ ለሚረሸናቸው የአማራ ወጣቶች “ቁጭትና ሃዘን ይሰማዋል” ብላ ነበር የጠበቀችው።
የብርሃኑ ነጋ ምላሽ “እዚህ ውስጥ ሲገቡ ይህ እንደሚመጣ አያውቁም ነበር ወይ?” የሚል ጥያቄ ነበር።
ገነት አራጌ “እነዚህ ሰዎች ጠመንጃ ይዘው እየተዋጉ አልነበረም። መሳሪያ በጃቸው በቤታቸው አልተገኘም። “ማህበረሰቡን ለማሸበር” በሚል እሳቤ ነው ከቤታቸው አውጥተው የረሸኗቸው። አንተ እንደምትለው የገቡበት ነገር” የለም።“ ብላ ለብርሃኑ ነጋ የሰጠችው ምላሽ፤ የአማራ ጥላቻና የስልጣን ጥም ልቡን ላደነደነው የሰው ጉድ ትርጉም አልነበረውም።
ገነት አራጌን ጨመሮ ዶ/ጫኔና ሌሎችም በገፍ የተሳሩ የቀድሞ የኢዜማ አባላት ሌላ ምንም ወንጀል የለባቸውም። የታሰሩትና የሚታሰሩት አማራ በመሆናቸው ብቻ ነው። በአማራ ላይ ያነጣጠረን የብርሃኑ ነጋን እና የአብይ አህመድን እርኩስ ጋብቻ ስለተቃወሙ ብቻ ነው። እነዚህ የቀድሞ የኢዜማ አባላት እየተሳሩ ያለውም፤ በዶ/ር ጫኔ እስራት ወቅት ኢዜማ ካወጣው መግለጫ በመነሳት “በኢዜማ ጠቋሚነትና ተባባሪነት ነው” ብል እያጋነንኩ አይደለም።
ለዚህ ክሴ የሰንድ መሳረጃ ማቅረብ አያስፈልገኝም። ዜጎችን፣ ልብ በሉልኝ አማሮችን አላልኩም፣ የራሱን የኢዜማን ቋንቋ ነው የምጠቀመው፤ በጅምላ በድሮን እና በከባድ መሳሪያ ከሚጨፈጭፍ፣ ዜጎችን በጅምላ ከሚያስር፣ ፍትህን መቀለጃ ካደረገ፣ ሃገርን ከመቼውም ዘመን በላይ ከሚዘርፍ ጨካኝ አገዛዝ ጋር ተባብሮ የሚሰራ ኢዜማ ከአብይ እኩል ተጠያቂ የማይሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም።
ገነት አራጊ በታጣቂዎች ከቤቷ ከተወሰደች 45 ቀናት አልፏታል። ቤተሰቦቿ በህይወት ትኑር አትኑር የሚያውቁት ነገር የለም። በከተማው ውስጥ በሚገኙ እስርቤቶችና ማጎሪያዎች ተዘዋውረው ሊያገኛት አልቻሉም። ከዚህ ቀደም ታስራ በነበረበት ወቅት ከባድ ድብደባ ተፈጽሞባት ነበር። አካላዊ ቁመናዋ የአብይን አህመድ ባለጌ አፋኞች ጡቻና እርግጫ መቋቋም የሚችል አይደለም። ምን አድርገዋት ይሆን? ወላጆቿን ብቻ ሳይሆን የምናውቃትን ሁሉ የሚያሳስብ ነው።
ጌታው ብርሃኑ ነጋ ሆይ! የዚች ወጣት ሴት ቤተሰቦች ለአንተ ክብር በቤታቸው በደገሱት ድግስ ላይ እኔም ታድሜ ፍቅራቸውን የገለጹበትን ምሽት አስታውሰዋለሁ። የገነትን ጉዳይ እንደተለመደው “እዚህ ውስጥ ስትገባ ይህን እንደሚከተል አታውቅም ነበር ወይ” በሚለው ራስን መሸንገያ አመክኖህ ስቃይዋን እያወቅህ እንዳላየህ እለፈው። ግድ የለም። ሌላው ቢቀር እነዛ እንደዛ ያከበሩህና ፍቅራቸውን የገለጹልህ ወላጆች፣ ለ45 ቀናት ልጃቸው የት እንደወደቀች ባለማወቃቸው የሚያነቡት የደም እምባ ግድ አይልህም?
ጌታው ብርሃኑ! ሁሉ ነገር ይቅር። ሰው እንዴት ያለማስረጃ ይታሰራል የሚል ጥያቄው ይቅር? ሰው እንዴት ፍርድ ቤት ሳይቀርብ 48ሰአት፣ አንድ ሳምንትና 14 ቀናት ያልፋሉ የሚለው የቅንጦት ጥያቄ ይቅር። “ገነት ታስራ ሰቆቃ ለምን ይፈጸምባታል” የሚል ቁጭት ይቅር።
ሆኖም ግን ለእነዛ እንግዳ ተቀባይና አከባሪ ወላጆቿ ስትል፣ ጌታህን አብይ ወይም አሽከሮቹን ጠይቀህ፣ “ልጃችሁ እዚህ ነው ያለችው” የምትል ትንሽ መልእክት ማስተላለፍ እስኪያስቸግር ድረስ ነወይ ስብእናህ ተንጠፍጠፎ ያለቀው? ምን አይነት ክፉ ዘመን መጣ?
ለገነት አራጌ፣ ከገነት አራጌ ጋር ከየቤታቸው ለታፈኑትና ለሌሎችም አማራ ብቻ በመሆናቸው ብቻ በግፍ ታስረው ለሚማቅቁት ወገኖቻችን ድምጻችንን እናሰማ
ይህን ጽሁፍ በማጋራት ተባበሩ