የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የመጨረሻው ጫፍ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከዕጥፍ በላይ ዋጋው ሽቅብ እየሄደ ነው፡፡ ነዳጅ ዋጋው በጨመረ ቁጥር ገበያውም አብሮ በዋጋ ጭማሪዎች ይሞቃል፡፡ ‹‹መንግሥት በነዳጅ መሸጫ ዋጋ ላይ ማስተካከያ አደረገ›› በሚል አርዕስት የተላለፈው ውሳኔ መሬት ላይ ሲወርድ የሸማቹን ኑሮ የበለጠ እየተናጋ ነው፡፡
እንደ ዋዛ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ተደረገ እየተባለ የሚተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ እየመጣ ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት በእጅጉ ያሠጋል፡፡ ከሁኔታዎች መገንዘብ እንደምንችለው የነዳጅ ዋጋ ከዚህም በኋላ ቢሆን የሚረግብ አይመስልም፡፡ መንግሥት ዛሬም በነዳጅ ምርቶች ላይ ድጎማ እያደረግኩ ነው ቢልም ድጎማው የዋጋ ጭማሪን አላረገበውም፡፡
በአንፃሩ፣ ‹‹መንግሥት የነዳጅ ዋጋ ላይ ማስተካከያ አደረገ›› ተብሎ እንደሚገለጸው፣ ‹‹መንግሥት ለሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ አደረገ›› የሚል የሕዝብ ማስታወቂያ በማይሰማበት ሁኔታ፣ ዜጎች እየተሰቀለ ያለውን የዋጋ ንረት ከማይቋቋሙበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ የነዳጅ ምርቶች ላይ ‹‹የዋጋ ማስተካከያ›› ተደረገ በተባለ ማግሥት ተደጋግመው ለሚፈጠሩ የዋጋ ጭማሪዎች ማካካሻ የሚሆን ነገር የሌለው ሸማች ኑሮን እንዴት ተቋቁሞ እንደሚዘለቅ ፈጣሪ ይወቅ፡፡
ባለፉት ተከታታይ ወሮች የተደረጉት ተደጋጋሚ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪዎች ምነው አንዴ ሆነው በተገላገልን የሚያስብሉ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል፡፡ ምክንያቱም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በታወጀ ቁጥር በነጋታው በደመ ነፍስ የሚደረግ የምርትና አገልግሎቶች ዋጋ ጭማሪዎች ያለማቋረጥ መተግበራቸው ሸማቹ ኢኮኖሚያዊ ላልሆነና ለተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ሰለባ እንዲሆን በማድረጉ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ የግብይት ባህሪ አንፃር የነዳጅ ዋጋ የቱንም ያህል የዋጋ ጭማሪ ቢደረግበት፣ በምርትና አገልግሎቶች ላይ የሚደረገው ጭማሪ ተደረገ ከተባለው የነዳጅ ጭማሪ ጋር ፈፅሞ የሚመጣጠን አይደለም፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥም የነዳጅ ዋጋ በጨመረ ቁጥር እየተደረገ ያለው የዋጋ ለውጥ ሲደማመር በወራት ልዩነት እየጨመረ የመጣው የነዳጅ ዋጋ ተደራራቢ የዋጋ ንረትን እያስከተለ ነው፡፡
ሰሞኑን በተደረገ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪም አንዳንድ ምርቶች አገልግሎቶች ላይ እየተደረገ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ተደረገ ከተባለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጋር የተገናዘበ ያለመሆኑን ያመለክተናል፡፡ አንድና ሁለት ምሳሌ ስናነሳ የትራንስፖርት ዋጋን እናስቀድም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ ከአውቶብስና ከመደበኛ ታክሲዎች ሌላ የሜትር ታክሲዎች በተለያዩ መስመሮች ላይ ተራ ጠብቀው እንደ ታክሲና አውቶቡስ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ ይታወቃል፡፡
እነዚህ ሜትር ታክሲዎች አገልግሎት የሚሰጡት በኪሎ ሜትር አሥልተው አይደለም፡፡ የራሳቸውን ዋጋ አውጥተው ከተለያዩ የታክሲና አውቶብስ መነሻ ጣቢያዎች ወደ ተለያዩ መዳረሻዎች የሚሰጡት የትራንስፖርት አገልግሎት ግን በሕግ ያልተፈቀደላቸው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ለምሳሌ ከጀሞ መገናኛ የሚሠሩ ሜትር ታክሲዎች አሉ፡፡ ለአንድ ሰው 150 ብር፣ ከጋርመንት ቦሌ 130 ብር፣ ከቃሊቲ ስታዲዮም 140 ብር ያስከፍላሉ፡፡
በእነዚህ መስመሮች ላይ የትራንስፖርት እጥረት ስላለ በተለይ ጠዋትና ማታ እነዚህን የሜትር ታክሲዎች ሳይወዱ በግድ የሚጠቀሙ ጥቂት የማይሆኑ ተገልጋዮች አሉ፡፡ የሜትር ታክሲዎች በሕግ በተፈቀደላቸው አሠራር በኪሎ ሜትር ቢሠሩ ሊከፈላቸው ይችል ከነበረው በላይ ስለሚያገኙበት ይህ ሥራ ጥሟቸዋል፡፡
በእንዲህ ያለ ዋጋ ሲያስከፍሉ የነበሩት ሜትር ታክሲዎች አሁን የሰሞኑን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳብበው ያደረጉት ጭማሪ ያስደነግጣል፡፡ ለምሳሌ ከጀሞ መገናኛ አንድ መቶ ሃምሳ ብር ያስከፍሉ የነበረውን በአንዴ 30 ብር የዋጋ ጭማሪ አድርገው 180 ብር አድርሰውታል፡፡ ይህ በመቶኛ ሲሠላ በአንዴ 35 በመቶ ጨምረዋል ማለት ይቻላል፡፡ በሌሎች መስመሮችም ተመሳሳይ ጭማሪዎች ተደርገዋል፡፡ የሰሞኑ ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ግን በመቶኛ ሲሠላ በመቶ ብቻ መሆኑ ሲታሰብ አጋጣሚዎችን በመጠቀም የሚደረግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አጠቃላይ ገበያውን እንዴት እንደሚያበላሽ መገመት አያቅትም፡፡ ቀድሞም ቢሆን 150 ብር ትክክለኛ ዋጋው እንዳልነበረ ማንም የሚረዳው ነው፡፡ ይሄ ሳያንስ ሰበብ ተገኘ ተብሎ በደመ ነፍስ የሚደረጉ ጭማሪዎች ችግሩ የመንግሥት የዋጋ ጭማሪ ብቻ ሳይሆን በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሰበብ እየተሠሩ ያሉ ሸፍጦች ማኅበረሰቡን የበለጠ እየጎዳ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ በአንድ ዘርፍ፣ በአንድ የጉዞ መስመር፣ በአንድ ተገልጋይ ላይ በ30 ደቂቃ ውስጥ የተደረገበት ጭማሪ ነው፡፡
መደበኛ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡትም ቢሆኑ መንግሥት በነዳጅ ጭማሪው ሳቢያ የሚያወጣውን አዲስ ትራንስፖርት ታሪፍ ሳይጠብቁ በራሳቸው መንገድ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ መሆኑንም መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ በብዙ መስመሮች ላይ ከአሥር ብር እስከ 20 ብር ዋጋ በመጨመር እየሠሩ ነው፡፡ መንግሥት ገና በቀጣይ ቀናት አዲሱን ታሪፍ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ሕጋዊ ባልሆነ ታሪፍ ተገልጋይ እየተጎዳ በመሆኑ አዲሱ ታሪፍ በቶሎ መተግበር አለበት፡፡
ከሰሞኑ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ አንድ ሌላ ምሳሌ ልጥቀስ፣ አንድ ማሽነሪ ለመግዛት ስምምነት ያደረገ ሰው በውለታው መሠረት ግዥው ከባንክ ጋር የተሳሰረ ነበርና 40 በመቶውን ክፍያ ይፈጽማል፡፡ 60 በመቶውን ክፍያ ለማስፈጸም ጉዳዩን እየጨራረሰ ባለበት ወቅት፣ ከማሽነሪ ሽያጩ ኩባንያ ቀድሞ ከተገባው ውል በማፈንገጥ ወደ አራት ሚሊዮን ብር የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ይገለጽለታል፡፡ ስለዚህ ይህንን ክፍያ መክፈል እንደሚገባውም ይነግረዋል፡፡
‹‹ለምን ይህ ይሆናል ተዋውለን ጨርሰናል፣ ይህንን ያህል ብር የምጨምርበት ምክንያት የለም፤›› ብሎ ሲሞግት፣ የተሰጠው መልስ፣ ‹‹ነዳጅ ስለጨመረ ነው›› የሚል ነው፡፡ ነገሩ ገና መቋጫ ባያገኝም ይህ የነዳጅ ጭማሪ ጉዳይ እንዲህ ያለ ያልተገባ ድርጊት ለመፈጸም ምክንያት እየሆነ መምጣቱ ያሳዝናል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር ስለሚችል ዋጋ ማስተካከያ ይደረጋል የምትል ሽወዳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋግሞ እየተሰማና ውል እስኪፈርስ መድረሳቸውን የሚነግረን ነገር አለ፡፡
የግዥ ስምምነቶች በነዳጅ ጨመረ ሰበብ ዋጋቸው እንዲጨምር መደረጉ አግባብ ባይሆንም ድርጊቱ ግን እየተፈጸመ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ደግሞ ተያያዥነት ያላቸው በመሆኑ፣ የዋጋ ጭማሪው በቅብብሎሽ ሁሉም ጋር የሚደርስ ይሆናል፡፡ የእነዚህ ሸፍጦች ተደማምሮ የሚወድቀው የመጨረሻው ተገልጋይ ላይ ይሆናል፡፡ ታች ያለው ተገልጋይ ግን ነዳጅ ስለጨመረ ለሚገጥምህ የዋጋ ጭማሪ ይሁንልህ ተብሎ የሚደረግለት የገቢ ጭማሪ የለም፡፡ ይህንን ጫና የሚቋቋመው ከዚህ ቀደም ሲከፍለው በነበረ ገቢ መሆኑ ሲታሰብ፣ ነገን ብንፈራ አያስገርምም አንድ ሰሞን በ500 ብር ደመወዝ ይህንን ሁሉ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩት እንዴት ነው ተብለው የተጠየቁ አባወራ ‹‹በአስማት›› ብለው የሰጡት ምላሽን ያስታውሳል፡፡
እየሮጠ ካለው የዋጋ ንረት ገቢያቸው ያልተስማማላቸው አንዳንድ መካከለኛ ገቢ አላቸው የሚባሉ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ልጆቻቸውን ቀለብ ይቅደም ብለው ከግል ትምህርት ቤት አውጥተው መንግሥት ትምህርት ቤት ያስገቡ ወላጆች፣ ይህንንም አድርገው አልቻሉም፡፡ መሰል ዕድል የሚጠባበቁም አሉ፡፡ የኑሮ ውድነቱ እዚህ ደረጃ እያደረሰን ነውና አሁንም ብልኃት የታከለበት መፍትሔ ካልተበጀ የነገው የኑሮ ውድነት የበለጠ ማሳሰቡ አይቀርም፡፡ በአንድ በኩል ችግሩን የመንግሥት ብቻ ማድረግም ተገቢ አይሆንም፡፡ ከምናያቸው ነገሮች እኛም የአኗኗር ዘይቤያችንን መቀየር ግድ መሆኑን እየነገረን ነው፡፡ ሥራው ከተገኘ ሁለትም ሦስትም ሥራ መሥራትን መላመድ ሁሉ ይኖርብናል፡፡
የመንግሥት ፖሊሲዎችም ዜጎች እየገጠማቸው ያለውን የኑሮ ጫና ማቃለል የሚችሉ ተጨማሪ ሥራዎች ይጠይቃሉ፡፡
ገቢን ለማሳደግ ደግሞ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ ምርትና ምርትን ለማሳግ መንግሥት ከዚሁ ጋር የተጣጣመ ፖሊሲ ያስፈልገዋል፡፡ አሁን ባለው የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ የሸቀጦችን ዋጋ በቀላሉ ማውረድ እንደማይቻል ኑሯችን እየነገረን በመሆኑ፣ ሁላችንም የመፍትሔው አካል በመሆንና ቢያንስ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ልናሟላበት የምንችለውን አቅም ለመፍጠር ግድ ይለናል፡፡
የዋጋ ንረትን ለማርገብ የተደረጉ ሙከራዎች ለምን ውጤት እንዳላመጡ በመገምገም፣ ከዚህ በኋላ ምን ይደረግ የሚለው ትልቁ ሥራ የመንግሥት የሚለው ሥራ የመንግሥት ቢሆንም፣ መፍትሔ አለን የሚሉ ወገኖች ሐሳባቸውን የሚቀርብበት ሁኔታ መመኘት ሁሉ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ እንደ አገር አጀንዳ ታይተው ሊሠራባቸው ይገባል፡፡