“ የታመሙብን፣ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ የማይችሉ ልጆች በመካከላችን አሉ ” – በማይናማር የኢትዮጵያውያን አስተባባሪ
በታጋቾች ተገደው ሲሰሩት ከነበረው ፋታ የማይሰጥ አስከፊ ስራ ወጥተው በማይናማር በተለያዩ ካምፕች በሚሊታሪ ቁጥጥር ስር ያሉ ኢትዮጵያውያን መንግስት በአፋጣኝ እንዲደርስላቸው ዛሬም በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል ተማጽነዋል።
ኢትዮጵያውያኑ ዛሬስ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምን አሉ?
አንድ ወጣት ፦
“ ለመንግስት የምናቀርበው ጥያቄ አለ። ትኬት መሸፈን የማይችል፤ እንደ ዜጋ የማይቆጥረን፤ ‘አልፈልጋችሁም’ የሚለንም ከሆነ፣ በኤንጂኦ በኩል እንኳ ወደ ሌላ ሀገር እንድንሻገር ግልጽ የሆነ ምላሽ እንፈልጋለን።
ወይ ፕሌን ልኮ ያስወጣን ካልሆነ ‘አልፈልጋችሁም፤ ዜጎቼ አይደላችሁም’ ብሎ ይካደን አማራጫችንን እንውሰድ፤ ይህን እንዲያደርግልን እንፈልጋለን ” ብሏል።
ሌላኛው ወጣት በሰጠን ቃል ፦
“ ባለንበት ቦታ ሁኔታዎች እየከበዱ ነው። ሲያሰሩን የነበረውን ሥራ ለቀን ከወጣን ከወር በላይ ሆነን። በጭንቀትና ድብርት ውስጥ ነን።
መንግስት እንደ ዜጋ የማይቆጥረን እና ‘ወደ ሀገር እንዲገቡ አልፈልግም’ የሚለን ከሆነ በግልጽ ይንገረን። በመንግስት በኩል ስለኛ እንዲህ ተብሏል እየተባለ አይደለም ” ነው ያለው።
ሌላኛው ወጣት በበኩሉ ፦
“ ሥራውን አቁመን ሌላ ካምፕ ከገባን 4ዐ ቀናት አልፎናል። እስካሁን ግን ወደ ኢትዮጵያ መመለሳችንን በተመለከተ ምንም ነገር የለም።
አብረውን ከነበሩ የ29 ሀገራት መካከል አብዛኛዎቹ ለዜጎቻቸው ያላቸውን ክብር በመግለጽ ወስወዋቸል። የቀረነው አብዛኞቻችን ኢትዮጵያውያን ነን።
መንግስት ‘አልፈልግም፤ ዜጎቼ አይደሉም’ ብሎ የሚክደን ከሆነ በኤንጂኦም ቢሆን ወደ ሌላ ሀገር ከዚህ መውጣት እንፈልጋለን። በግልጽ መንግስት ይጠየቅልን” ብሏል።
ሌሎች ሁለት ወጣቶች ደግሞ ፦
“ የኛን ባህልና ሃይማኖት የማይቀበለውን ምግብ ስንሰጥ ለመጣል እንገደዳለን። ለምሳሌ አሳማ ከሩዝ፤ የዶሮ ጣት ሳር ከሚመስል አትክልት ጋር ስንሰጥ ጥለን በጦም አንጀታችን እንውላለን።
ውሃ በጃር ነው የሚመጣው፤ የቀደመ ይቀዳል፤ ያልቀደመ በጥም አፉ ይደርቃል። የምግብና የውሃ እጥረት አለ። BDF ሚሊታሪ ካምፕ ውስጥ ነን። ብዛታችን 260 ኢትዮጵያውያን ነው።
እኛ ደግሞ ያለነው DKBA የሚባለው ካምፕ ውስጥ ነን። ብዛታችን 255 ኢትዮጵያዊ ነን። የምንመገበው በቀን አንድ ጊዜ ነው፤ በቂ የመጠጥ ውሃም አናገኝም።
የምናድረው ካርቶን አንጥፈን ወለል ላይ ነው። በዚህ ሁኔታ ከአንድ ወር በላይ ቆየን፤ ምንም አዲስ ነገር አልሰማንም። መጀመሪያ ከ21 ሀገራት ዜጎች በላይ ነበርን አሁን ሁሉም ሀገሮች እያስወጡ የ5 ሀገር ዜጎች ብቻ ቀርተናል። እነሱም በቅርቡ እንወጣለን ነው የሚሉት።
እኛ ግን ምንም መልስ አላገኘንም። በቆየን ቁጥር ምን እንደሚያጋጥመን አናውቅም ” ሲሉ ያሉበትን ሁኔታና ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በሌሎች ካምፓች የሚገኙ ከ480 በላይ ዜጎችም ተመሳሳይ ችግር እየገጠማቸው መሆኑ ተመልክቷል።
በማይናማር ያሉ ኢትዮጵያውያን አንድ አስተባባሪ ምን አለ ?
“ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ በጣም አስጨናቂ እየሆነ መጣና ብዙዎቹ እየተጨነቁብን ተቸግረናል። የወላጅ ኮሚቴ በጣረው ልክ ችግራችን ሊቀረፍ አልቻለም።
ጃፓን ኤምባሲ ወደ ኢትዮጵያ መሄድ ያለብንን ከ600 በላይ ልጆች ስም ዝርዝር ልኮ አፕሩቭ ተደርጎ ከተመለሰ በኋላ እንደገና ወደ ሚሊታሪ ደግሞ፥ ወደ ታይላይድና ኢትዮጵያ እንድንጓዝ መፃፍ ነበረበት። ያንን አላደረገም።
መንግስት ሂደቱን እያስኬደ ቢሆንም መጓተትና መዘግዬት አለ። በዚያ ምክንያት አራት የተመሙብን፤ ራሳቸውን ችለው የማይንቀሳቀሱ ልጆች በመካከላችን አሉ።
ሰርጀሪ የተሰሩ አሉ። እዚህ ደግሞ ሰርጀሪ መሰራት በጣም ከባድ ነው። ሀኪሞቹ ታማኝ አይደሉም። ሰርጀሪ የተሰሩ ልጆች ብዙ ችግር ደርሶባቸዋል።
ሁሉም ሰው ኪሱ ባዶ ነው። የሚቀርበው ምግብም ለመመገብ የማይሆን (ከእኛ የአመጋገብ ባህል ጋር አብሮ የማይሄድ) በመሆኑ ለመመገብ ተቸግረናል። ምግብ መግዛት፣ የታመሙትን ማሳከም አልተቻለም ” ብሏል።
ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በማይናማር ስላሉ ዜጎች ጉዳይ ተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አልተገኘም። ተቋሙ አሁንም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆነ እናስተናግዳለን።