የገዢው ፓርቲ አመራሮች ኢዜማን ለመወንጀል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም

🔴 ” ፀረ-ሠላም ሃይሎች በአንድ ሚሊሻ ቤት ላይ እሳት ለኩሰዉ የሁለት ጨቅላ ሕፃናት ሕይወት አልፏል “- የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ

➡️ ” የገዢው ፓርቲ አመራሮች ኢዜማን ለመወንጀል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ” – የወረዳው ኢዜማ ተመራጭ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ ጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዘይሴ ወዘቃ ቀበሌ የወረዳዉ አስተዳደር ” ፀረ ሰላም የኢዜማ ከባላትና አመራሮች ናቸዉ ” ባላቸዉ አካላት በአንድ የአከባቢዉ ሚሊሻ ቤት ላይ ሌሊት በተጣለ የእሳት አደጋ የሁለት ጨቅላ ሕፃናትን ሕይወት መቀጠፉን ገለጿል።

በአካልና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንም ወረዳው ገልጿል።

የወረዳዉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ሶፎንያስ ጥጦስ  ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል ፥ ” ጥቃቱ የተፈፀመዉ መጋቢት 19 ከሌሊቱ 5:30 ጀምሮ ነው የጥፋት ቡድኑ አስቀድሞ ተዘጋጅቶ በአካባቢዉ በአንድ የወረዳ አመራር ቤት ላይ አደጋ ለማድረስ ሞክሮ ነበር ” ብለዋል።

” በቀበሌዉ የተለያዩ ቦታዎች የተኮስ እሩምታ በመክፈት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በቀበሌዉ የአንድን ሚሊሻ ቤት በማቃጠል ላይ እያሉ ሚሊሻዉና አቅም ያላቸዉ የቤተሰቡ አባላት ሸሽተዉ በማምለጣቸዉ መሸሽ ያልቻሉ ሁለት የ7 እና 4 ዓመት ሕፃናትን ከነሕይወታቸው አቃጥለዋል ” ሲሉ ከሰዋል።

” ቡድኑ ከዚህ ቀደምም መሰል ጥቃቶችን ይፈጽም ነበር ” ያሉት አቶ ሶፎንያስ ” የጥፋት ቡድኑ አባላት ጫካ የመሸጉ የኢዜማ አባላትና አመራሮች ናቸዉ በአከባቢዉ የገዢዉን ፓርቲ አባላት እና አመራሮች ደግሞ ኢላማቸዉ ናቸው ” ሲሉ ተናግረዋል።

የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ቤት ኃላፊ አቶ ኮሜ ኮታ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፤ ” ከጥቃቱ አድራሾች አንዱ ተይዟል በአሁኑ ወቅትም መደበኛ ፖሊስ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አድማ ብተና እና የፌዴራል ፖሊስ በጋራ በመሆን በአከባቢዉን ተሰማርተዋል ጥፍተኛዉን ለሕግ የማቅረብና ሕዝቡንም የማረጋጋት ስራ እየሰሩ” ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ወረዳዉ ኢዜማ ፓርቲ ተመራጭና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ አማንያስ ክአን ደዉሎ ነበር።

እሳቸውም  ” ይህ ፍፁም ከእውነታዉ የራቀ የዉሸት ውንጀላ ነዉ ” ብለዋል።

” የዘይሴን ማህበረሰብ እርስ በርስ በማባላት በጋራ ቆሞ የጠየቀዉን የመዋቅር ጥያቄ ለማስቀረት የተሸረበ ሴራ ነዉ ” ሲሉም ገልጸዋል።

አቶ አማንያስ ፤ የገዢዉ ፓርቲ አመራሮች ሕዝቡ ኢዜማ ፓርቲን እንዲጠላ ደጋግመው የመወንጀል ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል።

” ይህም የዚሁ አካል ነዉና ገለልተኛ አጣሪ ቡድን በአከባቢዉ ያለዉን ግፍና ጭቆና ማጣራት ቢችል ጥሩ ነበር ”  ሲሉ ገልፀዋል።

” የገዢው ፓርቲ አመራሮች ኢዜማን ለመወንጀል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ” ሲሉንም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ዛሬ ባወጣዉ መግለጫ የተፈፀመውን ዘግናኝ ድርጊት አዉግዟል።

አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች እና የመንግስት አመራሮች ድርጊቱን ከፓርቲው ጋር ያያዙበትን መንገድ እንዲሁም የስም ማጥፋት ዘመቻ በቸልታ እንማይመለከት ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ እንደሚከታተል በመግለፅ ፓርቲዉ በእንደዚህ አይነት ህገወጥ ተግባር እንደማይሳተፍና ድርጊቱን የፈፀሙ አካላት በአፋጣኝ ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል።