ልጃችን በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ታፍና ከተወሰደች በኋላ ልትገኝ አልቻለችም

“ልጃችን በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ታፍና ከተወሰደች በኋላ ልትገኝ አልቻለችም”— የኢዜማ ተወካይ በመሆን ያገለገለችው የገነት አራጌ ቤተሰቦች ለመሠረት ሚዲያ

(መሠረት ሚድያ)- የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ/ም አዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ መነን ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከምሽቱ 2:00 ሰዓት ላይ ቀይ ቦኔት በለበሱ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ታፍና ከተወሰደች በኋላ አድራሻዋን ማግኘት አልቻልንም ብለው የኢዜማ ተወካይ የነበረችው የገነት አራጌ ቤተሰቦች ለመሠረት ሚዲያ ተናግረዋል።

ገነት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የብሔራዊ የሴቶች ጉዳይ ተጠሪ በመሆን ያገለገለች ሲሆን የእስሯ ምክንያትም ከዚሁ ጋር ይገናኝ ካልሆነ በስተቀር ሌላ የፖለቲካ ተሳትፎ የላትም ሲሉ ቤተሰቦቿ ገልፀዋል።

የገነት ቤተሰቦች የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቢሮ፣ የፌደራል ፖሊስ እና ሌሎች ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ይታሰሩበታል በተባሉ ጣቢያዎች አፈላልገን የነበረ ቢሆንም አድራሻዋ ሊገኝ አልቻለም ሲሉ ነግረውናል።

ገነት በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ታፍና ከተወሰደች ከ45 ቀናት በላይ መሆኑን መሠረት ሚዲያ አረጋግጧል።

የዛሬ አራት አመት ገደማ በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ወቅት ኢዜማ ያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው ገነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች የመጀመርያ ዲግሪ አግንታለች፡፡

በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓቶች ማእከል ያገለገለችው ገነት ኢዜማን ከተቀላቀለች በኋላ በወረዳ 17 በሴቶች ጉዳይ ተጠሪ በመሆን በምርጫ ወረዳው ሥራ አስፈፃሚ ሆና ሠርታለች፡፡