” የስነ ምግባር ግድፈቶች ተብለው በዝርዝር የተገለጹትን ተግባራት በቤተክርስቲያኒቱ መሪ መፈጸሙን አረጋግጠናል ” – ካውንስሉ
➡️ ” የበሻሻው ዐቢይ እና የሾለው ነብይ በተራ ጫጫታ ይጠፋሉ ብሎ ማሰብ ተራ ቅዠት ነው ” – ነቢይ ኢዩ ጩፋ
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በነብይ ኢዩ ጩፋ የሚመራውን የክራይስት አርሚ ኢንተርናሽናል ቸርች ማገዱን ይፋ አድርጓል።
በካውንስሉ የጽ/ቤት ሃላፊ ፓስተር ጌትነት ለማ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ የቤተክርስቲያኒቱን መታገድ ያረጋግጣል።
በካውንስሉ የምዝገባ ቁጥር 03111 በሃይማኖት ተቋምነት አባልነት የተመዘገበችው የክራይስት አርሚ ኢንተርናሽናል ቸርች ሊታገድ እንደሚችል ካውንስሉ ከሁለት ቀን በፊት በሰጠው መግለጫ ጥቆማ ሰጥቶ ነበር።
ካውንስሉ ” ቤተክርስቲያኒቱ የካውንስሉ አባል ስትሆን ልታከናውናቸው ከሚገቡ መመሪያዎችና ደንቦች መካከል አንዱ የካውንስሉ አባላት ስነ ምግባር መመሪያ ሲሆን በስነ ምግባር መመሪያው አንቀጽ 9.3 ላይ የስነ ምግባር ግድፈቶች ተብለው በዝርዝር የተገለጹትን ተግባራት በቤተክርስቲያኒቱ መሪ መፈጸሙን አረጋግጠናል ” ብሏል።
እግዱም በካውንስሉ ሥነ መለኮት ኮሚሽን እና የሕግ ኮሚሽን ታይቶ በሚመለከታቸው አካላት የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጡበት ድረስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ታግዳ እንደምትቆይ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከቀናት በፊት መግለጫ ሰጥቶ ነበር።
በወቅቱ መግለጫውን የሰጡት የካውንስሉ የጽ/ቤት ሃላፊ ፓስተር ጌትነት ለማ ” ዘይት መሸጥ እንደማይችሉ ከዚህ ቀደም ነግረናል አሁን ዘይት እየሸጡ ያሉ ተቋማት እና ግለሰቦች ዝርዝር መረጃዎች ተጠናቅሮ ደርሶናል በዚህ መሰረት በቅርቡ ተወስኖ ለሚዲያ ይፋ ይደረጋል ደንባችን ላይ በተቀመጠው መሰረት የሚገባውን ውሳኔ እናስተላልፋለን ” ብለው ነበር።
የክራይስት አርሚ ኢንተርናሽናል ቸርች መሪ ነብይ ኢዩ ጩፋ መጋቢት 11 ወደ ሃዋሳ ከተማ ሲገቡ የታየውን ትእይንት አስመልክቶ የተናገሩት ፓ/ር ጌትነት ” በጦር መሳሪያ ታጅቦ ወደ ከተማ የሚገባበት ሁኔታ የወንጌል አማኞችን አስተምህሮ በፍጹም የሚቃወም ነው እንቃወመዋለን ” ብለው ነበር።
በዝርዝር ባነሱት ሃሳብ ምን ብለው ነበር ?
” የመንግስት አካላት አንድ አገልጋይ ወደ ከተማ ሲገባ ፖሊስ አሰልፈው፣ መሳሪያ አስታጥቀው፣ አጀብ ፈጥረው ግርግር በማድረግ ከተማው ላይ ሌላ አካል የገባ እስኪመስል ድረስ ማድረግ ተገቢ ነው ብለን አናምንም።
ይህን ማድረጋቸው ለወንጌል አማኞች ክብር መስጠትም አይደለም የመቃብር ስፍራ አጥቶ የሚቸገር የወንጌል አማኝ ስላለ የመንግስት አካላት እሱን ያድርጉልን።
በተደጋጋሚ እንደዚህ የሚያደርጉ የተለያዩ ስያሜ ያላቸው አገልጋዮች ሊታረሙ ይገባል ብለን በጥብቅ ነው የምንቃወመው ፈጽሞ የወንጌል አማኞች ኢሜጅም አይደለም ።
በመሳሪያ ታጅቦ በዛ ሁሉ ግርግር ወደ አንድ ከተማ መግባት ምንድነው ትርጉሙ …ለእኛ ትርጉም አልባ ነው።
እንደዚህ አይነት ነገሮችን አስመልክቶ በቅርቡ መግለጫ እንሰጣለን መታገድ ያለባቸው ካሉም ይታገዳሉ በፍጹም ኮምፕሮማይዝ አናደርግም ምክንያቱም በካውንስሉ አብረን ስናመልክ ካውንስሉ ለእንደዚህ አይነት ነገሮች ጥላ ሆኖ አይደለም።
እንዲታረሙ፣ እንዲመለሱ ፣ እንዲስተካከሉ በተደጋጋሚ በፅሁፍ፣ በአካል ተነግሯቸዋል ሰርተፍኬት ሲወስዱ ፈርመዋል ይሄ ሁሉ ተደርጎ ‘ አንመለስም ‘ ብለው የዘይት ንግዳቸውን ከቀጠሉበት ዘይት መነገድ በካውንስሉ ፈቃድ ፈጽሞ አይቻልም።
ለሁሉም ክልሎች ይፋዊ ደብዳቤ ጽፈናል ቢጠየቁም እንኳን የመንግስት አካላት እንደዚህ አይነት መሳሪያ ይዞ ማጀብ ተገቢ አይደለም። ” ነበር ያሉት።
የካውንስሉን መግለጫ ተከትሎ ነቢይ እዩ ጩፋ በትላንትናው ዕለት በድምጽ መልእክት ሃሳባቸውን ሰጥተው ነበር።
በዚህም ” የክርስቶስ አምባሳደር ወደ ከተማ ይመጣል ተብሎ ማርሽ ባንድ ብቻ አይደለም ካላንደር ሊዘጋ ይችላል ፤ ገና መድፍ ይተኮሳል ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ነቢይ እዩ ጩፋ በዝርዝር ምን አሉ ?
” በመጀመሪያ የመንግስት ፓትሮል የሚወጣው ዌልካም ለማለት የሚወጣውን የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ነው ይህ የመንግስት ተቀዳሚ ሃላፊነት ነው በመቀጠል አምላክ የላከው አገልጋይ ወደ ከተማ ሲገባ ዌልካም ለማለት ነው የሚወጣው።
ከዚህ በኋላ ቪ8 ቶች (መኪኖች) ቪ8 ቶች ብቻ አይደለም በዚህ ዘመን የተፈጠረም ነገር ካለ ተጨምሮ አገልጋዮች ዌልካም ይባላሉ።
ለመቀበል እንደምትቸገሩ አውቃለሁ ነገር ግን ምርጫ የላችሁም አገልጋዮችን በንቀት አትዩ።
አገልጋዮች የእግዚአብሔር ድምጽ ፣ቃል አቀባዮች እና ምልክቶች ናቸው።
በማስፈራራት እና በማስጨነቅ ቀጥሎ የሚነሳውን ትውልድ ተስፋ ለማስቆረጥ የምትፈልጉ ሰዎች እኔ አለሁ ከዚህም በኋላ ፊት ለፊት ቆሜ ለሚመጣው ትውልድ በር ለመክፈት ከፊት አለሁ።
አንዳንድ ሰዎች ዘመኑ በሚመጥን መልኩ መንቀሳቀስን እንደ ሃጥያት ያያሉ።
ሰባት እና ስምንት ፓትሮል ለምን ይመደባል ? በዚህ ልክ መታጀቡ ለምን አስፈለገ ? የምትሉ ሰዎች ለአገልጋዮች መንግስታዊ የሆነ ጥበቃ ፣ ከለላ፣ ዌልካም ያስፈልጋል።
አንድ በእግዚአብሔር ለተሾመ አገልጋይ ምን ያህል ክብር እንደሚገባ መንግስት እና መንግስታዊ የሆኑ መዋቅሮች በተረዱበት በዚህ ጊዜ የቤተክርስቲያን መሪዎች አይናቸው መከደኑ ከምንም በላይ የሚያስገርም ነው።
ቪ8 በዛ፣ ፓትሮል በዛ የምትሉ ሰዎች እግዚአብሔር ባንተ ኮልኮሌ እንዲታጀብ ነው የምትፈልገው ? እግዚአብሔር በፓትሮል የሚታጀብ አምላክ አይደለም ፓትሮሉም ለኛ ነው እኛ ነን የምንታጀበው ከዚህ በኃላ።
ብታምኑም ባታምኑም በኢትዮጵያ ምድር በራሳቸው ጀት እየተንቀሳቀሱ የሚያገለግሉ አደገኛ ሰዎች ይነሳሉ።
የምታስተላልፉት መልዕክት ተስፋ ከመቁረጥ የመነጨ ይመስላል።
ሀዋሳ ስንገባ የተደረገልን አቀባበል ያስደነገጣችሁ ሰዎች ሰላም ናችሁ ? ለማንኛውም ከዚህ በኃላ በሚደረጉ ክሩሴዶች ከዚህ የበለጠ ነገር እንደሚሆን እንዳትጠራጠሩ ከወዲሁ አረጋግጥላችኋለሁ።
የበሻሻው ዐቢይ እና የሾለው ነብይ በተራ ጫጫታ ይጠፋሉ ብሎ ማሰብ ተራ ቅዠት ነው ” ብለዋል።
የካውንስሉን እግድ በሚመለከት እስካሁን ከቤተክርስቲያኒቱ የተሰጠ መግለጫ የለም።