“እንደ ትግራይ ጥለናችሁ ነው የምነወጣው” አበባው ታደሰ
ከአማራ ክልል ከሁሉም ዞን እና ወረዳዎች የተሰባሰቡ የብልፅግና አመራሮች በባህር ዳር ከተማ ሲመክሩ መቆየታቸው ይታወቃል። ስብሰባውን የመሩት አቶ አረጋ ከበደ ፣ ጄነራል አበባው ታደሰ እና ጄነራል መሐመድ ተሰማ ሲሆኑ አበባው ታደሰ ” መከላከያ ሰራዊቱን ያስጨረሰው የወረዳ እና የዞን አመራር ለፋኖ መረጃ እያቀበለ ነው። በጋራ እቅድ አውጥተን ስንቀሳቀስ ሰራዊታችን መንገድ ላይ የሚመታው እናንተ በምትሰጡት አቅጣጫ ነው። ከዚህ በኋላ ግን አመራሩን አንታገስም። ይህንን በሚያደርጉ አመራሮች ላይ ቀጥታ ወታደራዊ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ማስፈራሪያ አዘል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል::
መሐመድ ተሰማ በበኩላቸው “የሽንፈታችን ምክንያት እናንተ ናችሁ። የመጨረሻ እድል ነው የሰጠናችሁ” ሲሉ አክለዋል።
የወረዳ አመራሮች ወደ የመጡበት ሲመለሱ የዞን እና የክልል አመራሮች በጋራ ባደረጉት ስብሰባ እነዚሁ ሁለቱ የጦር ጄነራሎች እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ መርተውቷል።
ይህ ስብሰባ ደግሞ ቀደም ካለው ጉባኤ የሚለየው ጄነራል አበባው ታደሰ “ሰራዊታችን ለእናንተ ስልጣን እስከ መቼ ነው የሚሞተው? አመራሮቹ በጉጥ እና በሰፈር ተከፋፍላችሁ ስትነታረኩ ሰራዊታችን በየቦታው እያለቀ ነው። በዚህ ከቀጠላችሁ ግን እንደ ትግራይ ጥለናችሁ ነው የምንወጣው። ፋኖዎች መጥተው ቦታውን ይቆጣጠሩታል። በዚያን ወቅት የት እንደምትገቡ እናያለን። አሁንም አንድ እድል ሰጥተናችኋል። ሁል ጊዜ እናንተን ማጀብ እና መጠበቅ ሰልችቶናል። ዛሬውኑ እጀባውን ብናነሳ እና ሜዳ ላይ ብንበትናችሁ ፋኖ አንድ ቀን አያሳድራችሁም። ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።
አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው “የፖለቲካ እስረኞችን ፈትተን የተናጠል የተኩስ አቁም እንወጅ። ቀጥለን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን እንጠቀምበት” ሲሉ መፍትሄ ቢሆን ያሉትን ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል የብልፅግና ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው ” መፍትሄው ነፍጥ ካነገበው አካል ጋር በግልፅ መደራደር ነው ” ማለታቸውንም ሰምተናል።
ይህንኑ ስብሰባ እና ግምገማ ተከትሎ የክልሉ ሰላምና እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጄን ፣ የክልሉ ሚሊሻ ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ ከወንበራቸው ተገፍተዋል። የተገፉበት ምክንያት ደግሞ በእነአቶ አረጋ ከበደ ቡድን በኩል የቀረበው ግምገማ ሲሆን ሶስቱ የቢሮ ኃላፊዎች የሚመሩት የፀጥታ እና የሚሊሻ ኃይል ሕዝቡን በግልፅ እየዘረፈ ነው። ሰው አግቶ ገንዘብ ይቀበላል፣ ሴቶችን ይደፍራል፣ የሐይማኖት ተቋማትን ሳይቀር እያረከሰ ነው። ይህ ደግሞ መከላከያን ተገን በማድረግ በመሆኑ ሕዝቡ ጣቱን እየቀሰረ ያለው ወደ ሰራዊቱ ነው። ይህንን የቢሮ ኃላፊዎቹ ማስቆም አልቻሉም ይባስ ብለው ራሳቸው ኃላፊዎቹ በሚሊሻ እና በፀጥታ ኃይሉ ስም ገንዘብ እየመዘበሩ ነው። ክልሉ ባለመረጋጋቱ ምክንያት የኦዲት ቁጥጥሩ ስለላላ ይህንኑ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው በሌብነት ስራ ተሰማርተዋል ሲሉ ገምግመዋቸዋል።
በእነ አቶ አረጋ ከበደ ላይ የቀረበው ግምገማ ደግሞ አቶ አረጋ እና ቡድናቸው ይህንን ጦርነት የማስቆም አቅምና ችሎታ የላቸውም። ለፀጥታ የተመደበውን ገንዘብ ለብቻቸው ከቡድኖቻቸው ጋር እየመዘበሩት ነው የሚል ትችት ቀርቦባቸወዋል። አቶ አረጋ ከበደ የሚመሩት ካቢኒያቸው በሁለት ጎራ ተቧድኖ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የቆዬ ሲሆን አንዱ ቡድን የመንግስትን ጥግ ሌላው ደግሞ የፀጥታውን ተገን ይዞ ሲነታረክ መቆየቱም ታውቋል።
በዚሀ ምክንያት የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ተነስው ዶክተር እሸቱ የሱፍ ተሹመዋል። የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን ተነስተው የጄነራል አበባው ታደሰ የቅርብ ጓደኛ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የነበሩትን አቶ ዘላለም መንግስቴን ተተክተዋል።
ዘላለም መንግስቴ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ሆነው የወንጀል ምርመራውን ዘርፍ ሲመሩ መቆየታቸው ይታወቃል። በዚህ የስራ ዘመናቸው ከሰባት ሺህ አማራዎች በላይ ከፋኖ ጋር በተገናኘ በአዲስ አባባ፣ በሰመራ፣ በአዋሽ አርባ፣ በባቲ ቡርቃ ፣ በኮምቦልቻ ፣ በጎንደር እና በዳንግላ ወዘተ ምርመራ በሚል ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈፀምባቸው ቆይቷል። ለአብነትም የቀድሞው የኢንሳ ሰራተኛ ኢሳያስ በላይ በሰመራ ድብቅ እስር ቤት ውስጥ ተደብድቦ የተገደለው ዘላለም መንግስቴ በቀጥታ መመሪያ በሚሰጡት በኢንስፔክተር ተስፋዬ ኦላና ነው።
በቃሊቲ ፣ በአባ ሳሙኤል እና በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከ167በላይ የሚሆኑ የአማራ ምሁራን ፣ የምክር ቤት አባላት ፣ ጋዜጠኞች ፣ ጠበቆች እና ባለ ኃብቶች የውሸት ክስ ተመስርቶባቸው ለሁለት አመት ያህል በእስር እየመቀቁ ያሉት ዘላለም መንግስቴ በሚመሩት የወንጀል ምርመራ ቢሮ ስር ነው።