ከዚህ በፊት ታይቶም፣ ተሰምቶም በማይታወቅ በዋልያ ላይ ህገወጥ አደን እየተደረገ ነው

” ከዚህ በፊት ታይቶም፣ ተሰምቶም በማይታወቅ በዋልያ ላይ ህገወጥ አደን እየተደረገ ነው”

🟢 “ቁጥራቸውም ከ800 ወደ 306 አሽቆልቁሏል፣ የህልውና አደጋ ተደቅኖባቸዋል ” – ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ

በኢትዮጵያ ብርቅዬው የዋልያ አይቤክስ በሕገወጥ አደን ምክንያት ቁጥራቸው እየቀነሰ በመሆኑ በእጅጉ አሳሳቢ ሆኖብኛል ሲል የፌዴራል የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ናቃቸው ብርሌው የዋልያዎቹ ቁጥር እያሽቆለቆለ መሆኑን ያነሱ ሲሆን ከዚህ በፊት 800 ገደማ የነበረው ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ 306 ደርሷል ብለዋል።

ከዚህ በፊት የአደጋ መዝገብ ውስጥ ገብቶ የነበረው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፖርክ የዋልያዎቹ ቁጥር በመጨመሩ ከአደጋው መውጣት ችሎ ነበር ያሉት አቶ ናቃቸው፥ አሁን ግን ቁጣራቸው እየቀነሰ በመሆኑ የዳሰሳ ጥናት አካሂደናል ሲሉ ተናግረዋል።

የዋልያዎቹ ቁጥር ለምን ቀነሰ ?

” የህገ-ወጥ አደኖች ተበራክተዋል፣ የቁጥጥር ሥራው ላልቷል፣ የእሳት አደጋዎች በዝተዋል፣ በዚህ ችግር እጅግ በጣም ብዙ ዋልያዎችን አጥተናል፣ በዚህም 800 የነበረው ቁጥራቸው ወደ 306 አሽቆልቁሏል “ብለዋል።

ሥራ አስፈጻሚው፥ ” በሰሜኑ አካባቢ በነበረው ጦርነት ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ድምፅ ስለነበር ከቦታው አሽሽቷቸው ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ፣ በአካባቢው ያሉ ሰው ሰራሽ ችግሮች ናቸው ከፍተኛውን ድርሻ የሚይይዙት፣ የእሳት ቃጠሎው ጭምር።

ከዚህ በፊት ታይቶም፣ ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ በዋልያ ላይ ህገወጥ አደን እየተደረገ ነው፣ አደን የሚደረግባቸው ለምግብነት ይሁን ለሌላ ተያያዥ ጉዳዮች ለማወቅ በቀጣይ የጥበቃ፣ የቁጥጥር እና የክትትል ስራዎች ለማካሄድ ጥናት የሚፈልጉ ጉዳዮች በመሆናቸው እየተሰራ ነው ” ብለዋል።

አክለውም፥ ” ከዚህ በፊት ባደረግነው የዳሰሳ ጥናት የተገኙት ቅሪተ አካሎች ናቸው፣ በዚህም መነሻነት ነው ህገወጥ አደኖች መኖራቸው የታወቀው፣ ነገር ግን ለምግብነት ይዋሉ ለሌላ ተያያዥ ጉዳዮች ትክክለኛ የችግሩ ምክንያት ለማወቅ የዋልያ አንባሳደሮች ተለይተው ስልጠና ተሰጥቷቸው ዋልያን ተከታትለው የሚሰሩ አሉ ” ብለዋል።

ችግሩን ለመቀነስ ምን እየተደረገ ነው ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፦

“ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ይሄ ብርቅዬ እንስሳት ከመጥፋቱ በፊት ህልውናውን ልንታደገው ይገባል በማለት ብሔራዊ የዋልያ አይቤክስ ስትራቴጂ እያዘጋጀ ነው።

በተጨማሪም የጥበቃ እና ቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከአካባቢው ማህበረሰብ የተውጣጡ የዋልያ አንባሳደሮችን በመለየት ከእለት እለት የዋልያ ክትትል እንዲያደርጉ፣ ሬንጀሮችን ጨምርው  እንደሱ አይነት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።

ህልውናውን ለመታደግ ውስን የሰው ሃይል ለማሟላት ጥረት ተደርጓል፣ ህገወጥ ግጦሽንና ህገወጥ የመሬት ወረራዎችን ለመቆጣጠር ከአካባቢው መስተዳድር ጋር በመሆን እየተሰራ ነው።

የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል፣ በመሆኑም የብዙ አካላትን ተሳትፎ ይጠይቃል፣ የህግ አስከባሪዎችን ይመለከታል፣ ሙህራኖችን ይመለከታል፣ የአካባቢው ነዋሪን ይመለከታል፣ በአጠቃላይ የማይመለከተው ስለሌለ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ  ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ከወረዳ እስከ ፌደራል ላሉ አጋር እና ባለድርሻ አካላት ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከፍተኛ የማስገንዘብ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

የክትትል ስራ የሚሰሩ 8 የዋልያ አንባሳደሮች ተለይተው  ስልጠና ወስደው ዋልያ መገኛ በሆኑ ዋና ዋና ቦታዎች ተመድበው በብርቅዬ የዱር እንስሳት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።

በተመሳሳይ 8 ሬንጀሮች ተቀጥረው በልዩ ትኩረት በዚሁ የጥበቃ ሥራ ላይ መሰማራታቸው ተነግሯል።

በዋልያ መገኛ ቦታዎች የጥበቃ ስራውን ለማጠናከር ካምፖች ላይ የሰው ሃይል እንዲጨመር ሥራ እንዲሁም ልዩ የፖትሮል ቡድን በማዋቀር ህግ የማስከበር ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።