ፌደራል መንግሥቱ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን በማራዘም ዙሪያ ብቻውን እየሠራ ይገኛል ( ሕወሓት )

በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቋወመ።

ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ ፥ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚነንስትር  ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) የትግራይ ህዝብ  ለቀጣይ አንድ ዓመት ስልጣኑ የሚራዘመውን የጊዚያዊ አስተዳደሩን የሚመራ ፕሬዜዳንት እንዲጠቁም አስመልክቶ ያወጡትን መልዕክት ” የተናጠል ውሳኔና ተግባር ” ሲል ተቃውሟል።    

” የፕሪቶሪያ ሥምምነት ከተፈረመ ሁለት ዓመት ተኩል ሆኖታል ” ያለው የደብረፅዮን (ዶ/ር) ህወሓት ” ስምምነቱ በሙሉነት ተተግብሮ ትግራይ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ሊኖራት ይገባ ነበር ”  ብሏል። 

” የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በሙሉነት ያልተተገበረው የፌደራል መንግስት በስምምነቱ አፈፃፀምና አተገባበር በተከተለው የተሳሳተ አካሄድና ፓለቲካዊ ቀውስ እንዲፈጠር በመስራቱ ነው ”  ሲልም ክስ አሰምቷል።

” በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አንቀፅ 3 መሰረት ተዋዋይ ወገን ሌላውን በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ በፕሮፓጋንዳ ማጥቃት ይከለክላል  ይሁን እንጂ ይህንኑ የስምምነቱ አካል በፌደራል መንግስት በተደጋጋሚ እየተጣሰ ነው ” ብሏል።

” የፌደራል መንግስት ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መንፈስና ይዘት በወጣ አካሄድ አግባብነት በሌላቸው 359/1995፤ ደንብ 533/2015 ህግና አዋጆች እንዳሻው እየወሰነ ይገኛል ” የሚል ወቀሳም አቅርቧል።

” የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አንቀፅ 10 የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር በህወሓትና በኢትዮጵያ መንግስት መግባባት እንዲቋቋም ያዛል ” ያለው የደብረፅዮን (ዶ/ር) ህወሓት ” የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ውሳኔ መወሰን አይችልም ” ብሏል።    

” ህወሓት ፕሬዜዳንት ጌታቸው ረዳ ከስልጣን ማስነሳቱ ተከትሎ ፤ ጀነራል ታደሰ ወረደ ፕረዚደንት እንዲሆኑ ማእከላይ ኮሚቴ ወስኖ የኢትዮጵያ መንግስት ተቀብሎታል ” ያለም ሲሆን ” ይህንን ወደ ጎን በመተው በጠቅላይ ሚንስትሩ የተናጠል ውሳኔ በሚያስመስል  መልኩ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የሚጥስ አካሄድ ተቀባይነት የለውም ” ሲል ገልጿል።

” የፌደራል መንግስት ህዝብን ከሚጎዱ ግልፅ ተግባራት በመቆጠብ ዘላቂ ጥቅምና የጋራ ሰላም በሚያረጋግጡ ተግባራት እንዲያተኩር ጥሪ እናቀርባለን ” ያለው የደብረፅዮን (ዶ/ር) ህወሓት ” የተናጠል ውሳኔዎች እንዲቆሙ ” ብሏል።

ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት ሕወሓት፣ ፌደራል መንግሥቱ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን በማራዘም ዙሪያ ብቻውን እየሠራ ይገኛል በማለት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ከሷል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ውጤት እንጂ የፌደራል መንግሥቱ ብቸኛ ውሳኔ አይደለም ያለው ቡድኑ፣ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ አዲስ ፕሬዝዳንት በመሾም ዙሪያ በቅርቡ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ውይይት መደረጉንና የቡድኑ ማዕከላዊ ኮሚቴ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄኔራል ታደሠ ወረደ በጌታቸው ረዳ ምትክ በፕሬዝዳንትነት እንዲሾሙ መወሰኑን ገልጧል።

ኾኖም ከጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ዛሬ የቀረበው የዕጩ ፕሬዝዳንት ጥቆማ ጥሪ ይህንኑ የሕወሓት ውሳኔ ችላ ብሎታል በማለት ቡድኑ ወቅሷል። ቡድኑ አያይዞም፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት የመሾም ሥልጣን የጠቅላይ ሚንስትሩ ብቸኛ ውሳኔ እንዳልኾነ በመጥቀስ፣ የዕጩ ፕሬዝዳንት ጥቆማ ጥሪው የፕሪቶሪያውን ስምምነት ስለሚጥስ ተቀባይነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎታል።

ቡድኑ ይህን መግለጫ ያወጣው፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የትግራይ ሕዝብ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ዕጩ ፕሬዝዳንት ጥቆማ እንዲሠጡ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው።