እገታው ቀጥሏል፤ 40 ሰዎች ወደ አዲስ አበባ መግቢያ ሱሉልታ ላይ ታገቱ

በኦሮሚያ ከልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ከጎርፎ ከተማ ወጣ ብሎ ባለ ሥፍራ፣ ታጣቂዎች ትናንት ከቀኑ 10 ሰዓት ገደማ በሁለት ተሽከርካሪዎች ላይ በፈጸሙት እገታ 40 ያህል ተሳፋሪዎችን አፍነው መውሰዳቸውን ታውቋል ።

እገታው በተለምዶ ”ሃይሩፍ” ተብለው በሚጠሩ ሁለት መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ መፈጸሙን ምንጮች ተናግረዋል።


ተሽከርካሪዎቹ እገታው የተፈጸመባቸው ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ላይ ሳሉ ሲኾን፣ አንድ አይሱዙ የደረቅ ጭነት መኪና ደሞ ከታጣቂዎቹ እገታ ለማምለጥ ሲሞክር በተከፈተበት ተኩስ ጎማው ተመትቶ መገልበጡንና በተሽከርካሪው ላይ የነበሩ ሰዎች አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ዋዜማ ተረድታለች።

በዚሁ ዞን ከቀናት በፊት ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ከልል ሲያቀና በነበረ ”ፈለገ ግዮን” በተሰኘ አውቶቡስ ላይ በወረ ጃርሶ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት እገታ 60 ያህል ሰዎች ታፍነው መውሰዳቸውን ዋዜማ መዘገቧ ይታወሳል።