በዚህ ሳምንት አሊ ዶሮ ላይ የታገቱትን 58 ሰዎች ለመልቀቅ ታጣቂዎች በአንድ ሰው እስከ 1.5 ሚልዮን ብር እየጠየቁ ነው
(መረጃን ከመሠረት)- ከአራት ቀን በፊት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በፍቼ እና ጎሀፂዮን ከተሞች መሀል የታገቱትን 58 ዜጎች ለመልቀቅ ታጣቂዎች ከፍተኛ ገንዘብ እየጠየቁ እንደሆነ ታውቋል።
በአውቶቡስ ሲጓዙ ‘አሊ ዶሮ’ ተብሎ የሚጠራው ስፍራ ላይ ከታገቱት ዜጎች መሀል ህፃናት እና እድሜያቸው የገፋ አዛውንት እንደሚገኙበት ምንጮች ለመሠረት ሚድያ ጠቁመዋል።
መጋቢት 8 ቀን የተፈፀመው ይህ እገታ በመንግስት ሚድያዎችም ሆነ በባለስልጣናት ምንም ቃል ያልተተነፈሰበት መሆኑ እጅጉን እንዳሳዘናቸው የታጋች ቤተሰቦች ገልፀው አሁን ላይ የቻሉትን ለመሰብሰብ የየቤቱ እየዞሩ እየለመኑ እንዲሁም በሶሻል ሚድያ ለህዝብ የእርዳታ ጥሪ እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ መስመር ከዚህ በተደጋጋሚ እገታዎች የሚፈፀሙ ሲሆን በአካባቢው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላት በስፋት እንደሚንቀሳቀሱበት ይታወቃል።
“ተስፋችን ገንዘቡን ተበድረንም ሆነ ለምነን መክፈል ነው፣ ልጆቻችንን የሚያድንልን አካል አለ ብለን አናምን” ያሉ አንድ ወላጅ ወጣት ልጃቸው እቃ ለማምጣት አዲስ አበባ ሄዳ ስትመለስ እንደታገተች በእንባ ታጥበው ለሚድያችን አስረድተዋል።