አንድ የቀድሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሃላፊንና አንድ የቀድሞ የረድኤት ሠራተኛን ጨምሮ ስምንት የትግራይ ተወላጆች 12 የኢትዮጵያና ኤርትራ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ወታደራዊ አዛዦች በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በትግራይ “የጦር ወንጀል” እና “በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች” ፈጽመዋል በማለት ለጀርመን ዓቃቤ ሕግ አቤቱታ አቅርበዋል።
የወንጀሎቹ ሰለባና ወንጀሎቹ ሲፈጸም እማኝ የነበሩት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ የጀርመን ፌደራል ዓቃቤ ሕግ በወንጀሎቹ ላይ የምርመራ መዝገብ እንዲከፍትና በአገሪቱ ፍርድ ቤት ክስ እንዲመሠርት ጠይቀዋል።
ግለሰቦቹ አቤቱታውን ያቀረቡት፣ ሌጋል አክሽን ወርልድዋይድ በተሰኘ የሕግ ተቋምና ሌሎች ድርጅቶችና የሕግ ባለሙያዎች ድጋፍ ነው።
የጀርመን ዓቃቤ ሕግ በውጭ አገራት በተፈጸሙ ዓለማቀፍ አስከፊ ወንጀሎች ዙሪያ ምርመራ የማድረግ ሥልጣን አለው።