ህወሓት “አደብ እንዲገዛ መደረግ አለበት” – አቶ ባርጠማ ፍቃዱ፤ የኢዜማ የፓርላማ ተወካይ

ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 11፤ 2017 እየተካሄደ ባለው የፓርላማ መደበኛ ስብስባ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታን የተመለከተው ይገኝበታል። ገዢው ብልጽግና ፓርቲን በመወከል ከያያ ጉለሌ ምርጫ ክልል የተመረጡት ብርቄ ባህሩ፤ በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ “ወደ ግጭት እንዳያመራ” ያላቸውን ስጋት አንጸባርቀዋል። በክልሉ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ “ድጋሚ ዋጋ እንዳያስከፍለን ምን እየተሰራ ይገኛል?” ሲሉም ጥያቄቸውን ሰንዝረዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የእዣ ምርጫ ክልል የፓርላማ ተወካይ የሆኑት አቶ ባርጠማ ፍቃዱ፤ “ለትግራይ ሁኔታ የማዕከላዊ መንግስት እልባት ለምን አይሰጥም?” ሲሉ ተመሳሳይ ጥያቄ አንስተዋል። ህወሓት “እስከመቼ ሰላም እየነሳ ይኖራል?” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ህወሓት ባለው “የስልጣን ሱስ” “የትግራይ ህዝብን እረፍት በመንሳት”፣ “ሰላም እንዳይኖር የፕሪቶሪያ ስምምነት እየጣሰ ይገኛል” ሲሉ አቶ ባርጠማ ወንጅለዋል። እኚሁ የኢዜማ የፓርላማ ተወካይ የህወሓት ሰዎች “አደብ እንዲገዙ መደረግ አለበት” የሚል እምነት እንዳላቸው ሲናገሩ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈገግታ ሲያሳዩ ተስተውለዋል።

የፊደራል መንግስት የትግራይ ሁኔታን “ማስተናገድ ያለበት” በፕሪቶሪያ በተፈረመው ስምምነት “መሰረት” መሆን እንደሚገባው አቶ ባርጠማ አመልክተዋል። “ተደራዳሪ የፌደራል መንግስትን ጨምሮ፣ ብልጽግናን ጨምሮ፣ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ያካተተ፣ ክልሉን የሚመራ ጤነኛ አደረጃጀት መፈጠር ያለበትም ይመስለኛል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)