ፕሬዝደንቱ ላይ ያነጣጠረ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙ ታወቀ

የሶማሊያ መንግሥት አሸባብ በሀገሪቱ ፕሬዝደንት አጀብ ላይ ጥቃት ማድረሱን አረጋገጠ።

ታጣቂው ቡድን በትናንት ዕለት ከቀትር በፊት ፕሬዝደንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ላይ ያነጣጠረ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

የሶማሊያ መንግሥት ጥቃቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ፕሬዝደንት ሀሰን ከመቃዲሹ ተነስተው የሀገሪቱ ወታደሮች ወደተሰማሩበት ሺርሻባሌ ግንባር አካባቢዎች ታጅበው ሲጓዙ የቦንብ ፍንዳታው መከሰቱን አስታውቋል።

ጥቃቱ መክሸፉን ያመለከተው የሶማሊያ መንግሥት መግለጫ አክሎም ፕሬዝደንቱ ከጉዳት ተርፈው ካሰቡበት መድረሳቸውን ገልጿል።

ጥቃቱን የተመለከቱ ወታደሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች የፕሬዝደንቱ አጀብ መመታቱን የገለጹ ሲሆን፤ ከፕሬዝደንቱ መኖሪያ አቅራቢያም የአራት ሰዎች አስከሬን መመልከታቸውንም ተናግረዋል።

አሸባብ በተደጋጋሚ ሶማሊያ ውስጥ ጥቃት ሲያደርግ የቆየ ታጣቂ ቡድን ቢሆንም ከጎርጎሪዮሳዊው 2014 ዓ,ም ወዲህ በመሀሙድ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲፈጽም የትናንቱ የመጀመሪያው መሆኑ ነው የተገለጸው።

በተጠቀሰው ዓመት ሀሰን ሼክ መሀመድ በአንድ ሆቴል ውስጥ ንግግር እያደርጉ ሳለ አሸባብ ስፍራውን በቦምብ ማጋየቱ ተነግሯል።