” ከፍተኛ የሰራዊት ኃላፊ ‘ እንዴት ታሳልፉታላችሁ ‘ በሚል ደንፍቶ ፓትሮል ይዞ ኤርፖርት ድረስ እንደመጣ በኃላ ሰማን !! “

አቶ ጌታቸው ረዳ ለህይወታቸው የሚያሰጋ ችግር ገጥሟቸው ነበር ?

🚨 ” ከፍተኛ የሰራዊት ኃላፊ ‘ እንዴት ታሳልፉታላችሁ ‘ በሚል ደንፍቶ ፓትሮል ይዞ ኤርፖርት ድረስ እንደመጣ በኃላ ሰማን !! “

ካለፈው ሳምንት አንስቶ አዲስ አበባ የሚገኙት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ፤ ትግራይ በነበሩበት ሰዓት ደስ የማይሉ ነገሮች እንደነበሩ (ለአብነት የሰራዊት እንቅስቃሴ) ነገር ግን እሳቸው ለደህንነታቸው የሚያሰጋ ምልክት እንዳላዩ ተናገሩ።

ነገር ግን ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት መቐለ አሉላ ኣባነጋ ኤርፖርት 10:30 በሚሄዱበት ወቅት እሳቸው የማያውቁት ኬላ በሰራዊት አባላት ተዘርግቶ መንገድም ተዘግቶባቸው እንዳስቆሟቸው ፤ አጃቢዎቻቸውንም ጥያቄዎችን መጠየቃቸውን ጠቁመዋል።

ይህን ቃል የሰጡት ” ርዮት ” ለተሰኘ የማህበራዊ ሚዲያ በሰጡት ቃለምልልስ ነው።

አቶ ጌታቸው ረዳ በዝርዝር ምን አሉ ?

” አዲስ አበባ የተጠራሁት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው።

በአጋጣሚ function ውስጥ ባለሁበት ሰዓት ነው እሳቸው የሀገር ውስጥ ጉብኝት ላይ ነበሩ ‘ መገናኘት አለብን አንዳንድ ጉዳዮች በአካል ተገናኝተን መነጋገር አለብን ‘ አሉ።

ከዛ በፊት ማህተም መንጠቅ ዘመቻ እየተካሄደ ነበር። በብዙ መልኩ ይሄ ነገር እንዲቆም በተደጋጋሚ ጠይቄ ነበር። መተላለፍ ያለበትን ትዕዛዝ ህግን ተከትዬ ሰጥቼ ነበር ይሄ ሊሆን አልቻለም።

በዛ ሰዓት እኔ የአፄ ዮሐንስ ሙት ዓመት የሚከበርበት function ላይ ነበርኩኝ እዛ በነበርኩበት ሰዓት ቀደም ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ ነገ መገናኘት አለብን ‘ ብለው ስለነበር ትኬት ቆርጠውልኝ ጉዞ ጀመርኩ።

ከዛ በፊት አንዳንድ ደስ የማይሉ ነገሮች ነበሩ። የሰራዊት እንቅስቃሴ መቆም አለበት ብለን ጠይቀን (ስርዓት እስኪይዝ ነው የሰራዊት እንቅስቃሴ መቆም ያለበት) ሰራዊቱ እንደ ሰራዊት ሌላ የታለመለት ግብ አለ ፤ መስራት ያለበት ስራ ይኖራል ከዛ ውጭ ማህተም የመንጠቅ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት የለበትም የሚል ተደጋጋሚ ትእዛዞች ተጥሰው የሚደረጉ ደስ የማይሉ እንቅስቃሴዎች ነበሩ።

በግሌ ለደህንነቴ የሚያሰጋ እዚህ ግባ የሚባል ምልክት አላየሁም።

በእርግጥ ከማገኛቸው መረጃዎች አንጻር በዚህ ሂደት የተሳተፉት የሰራዊት አመራሮች ቀጣይ የኔን እንቅስቃሴ የመገደብ ፍላጎት እንደነበራቸው እሰማ ነበር ከነሱ እስካልሰማሁት ድረስ ከቁም ነገር አልቆጠርኩትም።

የጀመሩት ማህተም መንጠቅ፣ ‘ እገሌ ትክክለኛ ከንቲባ ነው ‘ ፣ ህገመንግስት የመተርጎም ኃላፊነት የተወሰኑ የጦር አመራር ነን የሚሉ ሰዎች ከያዙት በኃላ ጊዜያዊ አስተዳደሩን በተግባር የመቀየር ስራ ተጀምሯል።

እንቅስቃሴ መገደቡ ምናልባት ቢሮ እንዳልገባ ይሁን፣ አላውቅም ብቻ። ግን በይፋ ይህ ነው የሚባል ነገር ሰምቼ አላውቅም።

ከምክትሌም ጋር መገናኘት ካቆምን ረጅም ጊዜ ሆኖናል። እሳቸው ብዙ ጊዜ ስታይላቸውም ነው የሆነ ችግር ሲፈጠር ብዙ ጊዜ ስልክ ማጥፋት ወይም መራቅ ነው።

እኔ በዚህ ደረጃ ለህይወቴ የሚያሰጋ እዚህ ግባ የሚባል ነገር አለ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር።

ለማንኛውም ያኔ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ በምናደርግበት ሰዓት 10:30 መሰለኝ ኬላ እንደነበረ አላውቅም ኬላ ተደርጎ ነበር እንግዲህ እኔ በአጀብ ነው የምሄደው ኬላ ሲያስቆሙ የኔ ጠባቂዎች ‘ የምን ኬላ ነው ? ‘ የሚል ጥያቄ አቀረቡ።

አጃቢዎቼ ‘ የፕሬዜዳንቱ ነው መኪናው ‘ ሲላቸው ‘ አይ ማጣራት እንፈልጋለን እንደውላለን ‘ አሉ። ከዛ እኔ መስኮት ከፈትኩና ማን ጋር ነው የምትደውሉት የኔን ጉዞ በሚመለከት ስል እዛ አካባቢ ሲያስተባብር የነበረው ወጣት የሰራዊት ኃላፊ ይመስለኛል እኔን እንዳየ መከራከር አልፈለገም መንገዱን መንገዱን ከፍተውልን ሄድን።

ኤርፖርት ገባሁ። አውሮፕላን በምንሳፈርበት ሰዓት እዚህ ግባ የሚባል ምንም ነገር አልነበረም። አውሮፕላን ውስጥ ከገባን በኃላ የገባን ነገር ምንድነው የዛ አካባቢ ይሄን ኃላፊነት የወሰደ ከፍተኛ የሰራዊት ኃላፊ ‘ እንዴት ታሳልፉታላችሁ ‘ በሚል ደንፍቶ ፓትሮል ይዞ ኤርፖርት ድረስ እንደመጣ በኃላ ሰማን።

እኔ ምንም notice አላደረኩም ፓትሮል ይዞ መምጣት ብቻ ሳይሆን የፌዴራል ፖሊስ ለሚጠብቀው ኤርፖርት የፌዴራል ፖሊስን ጥሶ መግባት አይችልም ወይ ወደ ግጭት ይገባል። የኔም አጃቢዎች አሉ። ያኔ ወደ ግጭት ይገባል ወደ ግጭት ከተገባ የሚፈጠረውን ነገር እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በቁጥር የኔ አጃቢዎች የሚበልጡ ይመስለኛል። የኔ ጠባቂዎች ደስ የማይል ነገር እየተፈጠረ እንደሆነ ገምተዋል ግን መመለስና መሟገት አንችልም።

አውሮፕላኑ ተነሳ ሄድን።

አዲስ አበባ እንደገባን የነበረውን ሁኔታ ስናጣራ ኬላው ዝም ብሎ ተራ ኬላ እንዳልነበር (በነገራችን ላይ ምንም አይነት ኬላ መንግሥት ሳያውቀው መቀመጥ አይችልም) እዛ አካባቢ ያሉ የጦር ኃላፊዎች ብቻቸውን ያደረጉትም አልነበረም ከበላይ በተሰጠ ትእዛዝ ነው ኬላ የተደረገው።

ያ ፓትሮል ይዞ የመጣው የሰራዊት ኃላፊ የአየር መንገድ / አቬዬሽን security አባል ጋር ስልክ ደውሎ ‘ እሱ ብቻ ነው ? ወይስ ሌሎችንም ይዞ ነው እየወጣ ያለው ? ‘ የሚል ጥያቄ ሁሉ እንደጠየቀው አውቃለሁ።

ከዛ በኃላ ያወኳቸውን መረጃዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ምናልባት ጫን ያለ ስራ ለመስራት ፍላጎት እንደነበራቸው ፤ እንዲህ ያለው ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ምንም ነገር ባይፈጣር ጭምር እጅግ እጅግ አደገኛና ተቀባይነት የሌለው ተግባር እንደሆነ ብቻ ነው የማውቀው።

ከዛ እስከወጣሁበት ፤ አውሮፕላን ላይ እስከ ተሳፈርን ሰዓት ድረስ ኬላውን ጭምር አይቼ ይሄን ያክል ህይወቴን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሳይሆን ምናልባት የተለዩ እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ ከዛ ጋር የተያያዘ ነው የሚል እምነት ነበረኝ።

ከወጣሁ በኃላ የእነሱ ደጋፊዎች የሆኑ ስለማምለጤ በተደጋጋሚ ሲያወሩ ስሰማ ግን ምናልባትም አምልጬ መምጣቴ / ማምለጤ ነው የገባኝ ፤ ሀሳቤ የማምለጥ የነበር ባይሆንም። ደጋፊዎችቸው እና እነሱ የሚከፍሏቸው የሚዲያ ተቋማት ስለ ማምለጤ ሲያወሩ ምናልባትም ይዘውት የነበረ እቅድ መክሸፉን እራሳቸው ናቸው እያጋለጡ ያሉት እንጂ እስከዛ ድረስ የማውቀው አልነበረም። “