🔴 ” እጅ ከፍንጅ እናሲዛለን ግን በ3 ወር ውስጥ ይለቀቃሉ ” – የስብሰባ ተሳታፊዎች
➡️ ” የእኛ ሰራተኞች ፍጹም ናቸው አንልም አሁንም ብዙ ችግሮች አሉ ይህንን ችግር ለማስተካከል ክፍት ሆነን እየሰራን ነው ” – የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ
ከአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት እና ከነጋዴ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሰኞ ምሽት የተላለፈው ውይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ ከታሳታፊዎች ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከነጋዴው ማህበረሰብ ምን ምን ጥያቄዎች ተነሱ ?
” ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ የመስሪያ ቤቱን ስም የሚያጠለሹ የእናንተ መስሪያ ቤት ሰራተኞች አሉ።
ሁሉንም እያልን አይደለም ስነ ምግባር ያላቸው አመራሮች እንዳሉ ሁሉ ብልሹ አሰራር ውስጥ የተዘፈቁ ሰራተኞቻችሁ አሉ።
ብልሹ አሰራር ውስጥ የተዘፈቁትን እጅ ከፍንጅ እናሲዛለን ግን በ3 ወር ውስጥ ይለቀቃሉ።

አሁንም ድርድር እና ሩጫ መርካቶ ላይ አለ መጠኑ አንሷል እንጂ በጭቆ የመሄድ ነገር አሁንም ይታያል። … ይሄንን እንዴት አስታርቃቹ ትሄዳላቹ ?
የውጭ ሃገራት የሃገር ውስጥ ምርት የሆኑ ምግቦች ላይ ቫት አይጠየቅም እኛ ጋር ሚዛኑን ያልጠበቀ ዝቅተኛ እና ከፍተኛ ግምት እየተሰጠው ጎን ለጎን እንኳን ሰርቶ እንዳይበላ የሚያደርጉ ነገሮች ይፈጠራሉ። ሸቀጥ ላይ ቢቻል ቫት የሚነሳበት መንገድ ቢመቻች። “
… የሚሉ እና ሌሎችንም ጥያቄዎች አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ ምን ምላሽ ሰጡ ?
” የእኛ ሰራተኞች ፍጹም ናቸው አንልም አሁንም ብዙ ችግሮች አሉ ይህንን ችግር ለማስተካከል ክፍት ሆነን እየሰራን ነው፤ የሚመጣልንን ጥቆማ መሰረት አድርገን ችግሮችን ለመቅረፍ ዝግጁ ነን።
አላግባብ የሆነ ተቀባይነት የሌላቸው ወጪዎችን አንረው የሚያመጡ ሰዎች አሉ ኤክስፔንሱን ከፍ በማድረግ ፕሮፊቱን ለማሳነስ ተቀባይነት የሌላቸው ወጪዎችን አንሮ በማምጣት ለድርድር በር የሚከፍቱ አሉ።
ባንክ ላይ ያለ ትራንዛክሽን አብዛኛው ነጋዴ የቼክ አካውንት ኖሮት ሲያበቃ የቼክ አካውንት ላይ ያለውን ገንዘብ በአግባቡ ማኔጅ አያደርግም ።
የቼክ አካውንት ውስጥ ያለ ገንዘብ ዝም ብሎ አይወጣም ዝም ብሎም አይገባም የሚገባው በተሸጠው እቃ ልክ መሆን አለበት ሲወጣ ገንዘቡም ለምን አላማ እንደተከፈለ መረጃ መቅረብ አለበት አሁን ትልቁን ችግር እየፈጠረ ያለው ይሄ ነው።
ኦዲተሮች ባንክ ላይ የወጣ የገባውን እና ሂሳብ ላይ ያለውን ገንዘብ ሲያስተያዩ አይገናኝም።
በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ባንክ አካውንቱ ላይ ይታያል እዚጋ ግን ምንም አላተረፍኩም ብሎ ያመጣልናል።
ወይም የገባውን ገንዘብ ህጋዊነት በሌላቸው ጉዳዮች ወጪ ያደርጋል ማስረጃ አቅርብ ሲባል አይችልም ለድርድር እራሱን አጋልጦ ይሰጣል።
የሚመጣው የሂሳብ መዝገብ ፕሮፌሽናል ባልሆኑ ሰዎች እየተዘጋጀ ነጋዴው ችግር ውስጥ እየገባ ነው።
75 በመቶ የሚሆነው ነጋዴ ይዞ የሚመጣው የሂሳብ መዝገብ ደረጃውን ያልጠበቀና ሙያው በሌላቸው ግለሰቦች የሚዘጋጅ በመሆኑ ተቀባይነት አያገኝም።
ጥቅምት ላይ ባደረግነው የቅድመ ኦዲት ስራ የሂሳብ መዝገባቸውን ይዘው መጥተው የሂሳብ መዝገባቸው ተቀባይነት ያገኙ ነጋዴዎች 25 በመቶ አይሆኑም።
ከቫት ጋር የተገናኙ እና ውሳኔ የሚፈልጉ እንደዚህ እንደዚህ አይነት ዘርፎች ቫት ውስጥ ባይገቡ ይሄ ይሄ ደግሞ ቢወጣ የሚለውን የተወሰኑትን አስተያየቶች አደራጅተን ልከናል።
ቫት ውስጥ የሚገቡትን እና የማይገቡትን ምርቶች የመወሰን ሥልጣን ያለው የገንዘብ ሚኒስቴር ብቻ ነው ጥያቄዎቹ ተይዘዋል የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ያለው የገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑ መታወቅ አለበት ” ብለዋል።