🔴 “ እዚሁ አፍንጫችን ሥር ጀሞ አደባባይ ሸገር ሲቲ ላይ ሹፌሩን ደብድበው በደረሰኝ 3,000 አስከፍለውታል ” – ማኀበሩ
➡️ “ በአንድ ኬላ ከ2000 እስከ 5000 ብር እንጠየቃለን። በሀገሪቱ 280 ሕገ ወጥ ኬላዎች አሉ ” የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች
በተለያዩ ቦታዎች ባሉ ኬላዎች እስከ 5000 ብር ክፍያ እንደሚጠየቁ፣ ካልከፈሉ ማለፍ አለመቻል ብቻ ሳይሆን ድብደባና እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን አሽከርካሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ምን አሉ ?
“ የኬላ ላይ ሰቆቃ በተለይ በአማራ ክልል አልተቀረፈም። በኦሮሚያም በአንዳንድ ቦታዎች ሙሉ ለሙሉ አልተነሳም። በአንድ ኬላ ብቻ ከ2000 እስከ 5000 ብር እንጠየቃለን። በሀገሪቱ ከ280 በላይ ሕገ ወጥ ኬላዎች አሉ።
በመጀመሪያ ደረጃ ኬላዎች ላይ ሚሊሻዎች ተግባራቸው ሊሆን የሚገባው ሁከት እዳይነሳ መጠበቅ እንጂ፣ ፍቃድ አለው የለውም የሚለው አይደለም። ምክንያቱም ስራውን ስለማያቁት።
ይሄ ቫት ተቆርጦበታል ይሄነው ፍቃዱ ስንላቸው ፍቃዱንም አይቶ የመረዳት አቅም የላቸውም። የማያነቡ ሰዎች ሁሉ አሉ። ጅቡቲ ጭነን መጥተን በእግሊዝኛ የተፃፈ ብንሰጠው እኮ ለማንበብ የሚፋጠጥ አለ። ቢያስ ኬላ የሚቀመጡት የተማሩ ይሁኑ።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክና የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሮች ’28ዐ ሕገ ወጥ ኬላዎች አሉ፤ ይነሱ እያሉ ነው’ በፓርላማ ደረጃ። እነዚህ ሰዎች ተከታትለው ይህንን ካላስተገበሩ ስልጣናቸው ምኑ ላይ ነው ? ” ሲሉ ጠይቀዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያም፣ አሽከርካሪዎች የሚያነሱትን ቅሬታ ይዞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምን እየሰሩ እንደሆነ፣ ችግሩ ለምን እንዳልተቀረፈ የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪ ማኀበርን ምላሽ ጠይቋል።
የማኀበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ምን መለሱ ?
“ ሹፌሮች በሀገር ኢኮኖሚ የሚያደርጉት አስተዋፆ በተመቻቸ ሁኔታ አንዲያሽከረክሩ ነው የምንሰራው። ነገር ግን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የተለያዩ ችግሮች ይፈጠራሉ። የችግሮቹ ገፈት ቀማሾችም አሽከርካሪዎች ናቸው፤ የማህበረሰብ ጉዳት አንዳለ ሆኖ።
የመንግስት ስራ ትልቅ ቢሆንም አሁን ትልቁ ችግር ክልሎች ለፌዴራሉ መንግስት አይታዘዙም። ለምሳሌ ሞጆ ከተማን በተደጋጋሚ አናግረናል። ነገር ግን ማቆም አልቻለም።
ድሬዳዋ ከተማ ነበር የኮቴ ክፍያን ያስጀመረው ‘600 ብር’ ብሎ። ማቆም አልቻሉም አሁንም ሌሎች በመሀል እያቆሙ ቢሆንም። አሁንም አለ እዚሁ አፍንጫችን ሥር ጀሞ አደባባይ ሸገር ሲቲ ላይ ሾፌሩን ደብድበው በደረሰኝ 3,000 አስከፍለውታል። የተደበደበው ልጅ ደረሰኙን ይዞ እኛ ጋር መጥቷል።
ከሳምንት በፊት ሞጆ ከተማ ሲያልፍ ‘ጥሰኸን ሄደሃል’ በሚል በፓትሮል ተከትለው ሾፌሩን ደብድበው ፈንክተውት ከነ ደሙ ነው ቢሯችን የመጣው ይህ እነዚህ አካላት ባለመታዘዝ የሚያደርሱት ድርጊት ነው።
ለምሳሌ በቅርቡ እንደሚታየው የኬላ ክፍያ (የኮቴ ክፍያ)የሚባለው ቢቀዛቀዝም አልቆመም። ይህንን ማቆም ከባድ ነው በውስጡ ብዙ ውስብስብ የአሰራር ችግር ስላለበት ማስቆም አልተቻለም።
ነገር ግን ደግሞ አፋር ክልል በተደጋጋሚ ሄደን በመነጋገር አንድ ችግር ሲፈጠር እጅ ከፍንጅ ይዘው ችግር የሚፈጥርን ግለሰብ አስረው ይደውሉልናል። ማኀራችን አሁን በሰፊው እየሰራ ነው ያለው።
በተቻለ መጠን መንግስት እንደ መስሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን በፓርቲ ደረጃ የአሽከርካሪዎች ከፍተኛ ጥበቃና ከለላ እንዲደረግላቸው ጥረት እያደረገ ነው። ይህንን በቅርብ እናውቃለን ” ብለዋል።