አደገኛው የቤንሻንጉል ጉምዝ ብልፅግና ሹሞች አካሄድ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሶ ዞን የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ያለመከሰስ መብታቸው በተነሳባቸው የክልሉ ምክር ቤት አባል ዮሃንስ ተሠማ ላይ ዛሬ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንደፈቀደ ከቤተሰባቸው መስማቱን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። ተከሳሹ የተጠረጠሩባቸውን ወንጀሎች እንዳልፈጸሙ ለችሎቱ መናገራቸውንና “ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር” በሚል የቀረበባቸው ውንጀላ የትኛው የውጭ ኃይል እንደኾነ በግልጽ አልተገለጠም በማለት ለችሎቱ ምላሽ መስጠታቸውን ዘገባው ጠቅሷል። በተያያዘ፣ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ፣ የክልሉ ሕገመንግሥት ማሻሻያ ከምርጫ ክልሎች አደረጃጀት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም በማለት ለክልሉ ቴሌቪዥን በሠጠው ማብራሪያ ተናግሯል። ቢሮው፣ የሕገመንግሥት ማሻሻያው ያስፈለገው የክልሉ ምክር ቤት “ሕብረ-ብሔራዊ እና አካታች” እንዲኾን ለማስቻል እንደሆነ መግለጡን ጣቢያው ጠቅሷል። የሕገመንግሥታዊ ማሻሻያው መነሻ ሃሳብ የክልሉ ካቢኔ መኾኑን የጠቀሠው ቢሮው፣ ምክር ቤቱ የሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመራጮች በተገኙበት በአብላጫ ድምጽ ማሻሻያውን ማጽደቁን አብራርቷል ተብሏል። የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ ብዛት ከ99 ወደ 165 ማደጉን በመቃወም፣ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የሕገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ አቤቱታ ያስገቡት የተቃዋሚው ቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አባል ዮሃንስ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ከሳምንት በፊት መታሠራቸው ይታወሳል።