የሰላሌ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ቅሬታና የዩኒቨርስቲው ምላሽ!
🟢 ” መስቀል ማድረግ አንችልም፣ ነጠላ መልበስ ቀርቶ በላስቲክ መያዝ አይቻልም፣ ቅሬታ የሚያቀርብ ተማሪ እየታሰረ እያስፈራሩ ነው “- የተማሪዎች ቅሬታ
🟢 ” በግቢው ውስጥ እኔ ሳላውቃቸው የተፈጠሩ ችግሮች ካሉ አሁንም ቢሆን የተማሪዎችን መብት ለመጠበቅ እንሰራለን “- ዶክተር ገናናው ጎፌ የዩኒቨርስቲው ፕረዚዳንት
ሰላሌ ዩኒቨርስቲ የሚማሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ተማሪዎች በአሁኑ ዐብይ ፆም ላይ የመመገቢያ ስዓት እንዲሻሻልላቸው ወይም የሚመገቡትን ምግብ በራሳቸው እቃ ማውጣት እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው ቢጠይቁም መፍትሄ የሚሰጣቸው አካል ባለመኖሩ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።
በዩኒቨርስቲው ውስጥ ነጠላ መልበስም ሆነ በላስቲክ ይዘው እንዳይገቡ እና እንዳይወጡ ከመድረጉም በላይ ሀይማኖታቸውን የሚገልፅ መስቀል በአንገታቸው አርገው እንዳይታዩ መከልከላቸውን ተማሪዎቹ ተናግረዋል።
አክለውም ጥያቄያቸው ለብዙ ዓመታት የቆየ መሆኑን ገልፀው በየጊዜው የተለያዩ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጥያቄያቸውን ምላሽ ለማሰጠት በሚጠይቁበት ስዓት እናስተካክላለን የሚሉ የሽንገላ መልሶች ሲሰጥ መቆየቱንም ገልፀዋል።
ቅሬታቸው ምንድን ነው? በተማሪዎቹ አንደበት
” እኛ የጠየቅነው እስከ 9 ሰዓት ስለምንጾም 9 ሰዓት የመመገቢያ ካፍቴሪያችን ይከፈትልን ወይም የምንመገበውን ምግብ ምሳ ስዓት ላይ በራሳችን እቃ እንዲናወጣ ይፈቀድልን ነው፤ እና ቁርስ ስለማንመገብ የራሳችን እስከሆነ ድረስ ማውጣት ይፈቀድልን ነው፣ ነገር ግን ዩኒቨርሲቲው ዝምታን መርጧል።
በመሆኑም ላልተፈለገ ወጪ እና እንግልት እየተዳረግን ነው። ጥያቄ የሚያቀርብ ተማሪ በዩኒቨርሲቲው ፖሊሶች በሽጉጥ እስከማስፈራራት እየደረሰበት መሆኑን ገልፀዋል።
ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገው የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ቅሬታቸውን ከተማሪዎች ህብረት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርስቲው ፕረዝዳንት ድረስ ማቅረባቸውን ተናግሮ መፍትሄ ሳይሰጣቸው መቆየቱን እና ጥያቄ የሚያቀርቡ ተወካዮች ያደረጉት የተለየ ነገር ሳይኖር እየታሰሩ የዲሲፕሊን ጥያቄ ውስጥ እየገቡ ይገኛሉ ሲል አስረድቷል።
የአራተኛ አመት ተማሪ የሆነችው ሌለኛዋ ተማሪ ደግሞ አሁን ያሉበት ሁኔታ ለመናገርም ለመጠየቅም እንደማይቻል ገልጻ ሁሉም ነገር እንደ ፖለቲካ አጀንዳ እየተቆጠረ ተማሪዎች እየታሰሩ መሆኑን ገልጻለች።
ዶርም ውስጥ የእምነት መጽሐፎችን ጭምር ድምፅ ሳያወጡ ማንበብ ጭምር መከልከላቸውን በመግለጽ በዚህ ረገድ ችግር ውስጥ ነን ስትል ትናገራለች።
ተማሪዎቹ ለዩኒቨርሲቲው በፅሁፍ ቅሬታ ሲያቀርቡ ተወካይ መርጠው ተወካዩ ፈርሞ እንዲያስገባ እንደሚጠየቁ ገልፀው፤ በፈረመው ተወካይ ተማሪ ላይ የእስር እና የተጠያቂነት ጫና በማድረስ የሞራል ጉዳት ያደርሱበታል ብለዋል።
በተጨማሪም ከትናንት በፊት ቅሬታቸው እንዲሰማ ቁርስ ባለመመገብ ሲገልፁ እንደነበር የተናገሩ ሲሆን አንድ ተማሪ ተመርጦ በመታሰሩ “ጥያቄያችን የሁላችንም ነው ለምን ተለይቶ ይታሰራል” በማለት ልጁ በታሰረበት ቦታ በመገኘት ሲጠይቁ በቦታው የነበሩት የፌደራል ፖሊሶች “ምንም አታመጡም፣ ከፈለጋችሁ ግቡ እናንተም ታሰሩ” የሚሉ ምላሾችን እንደሰጧቸው ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ምን አሉ?
የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ገናናው ጎፌ “ቅሬታዎቹ ከዚህ በፊትም ነበሩ ያሉ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት ግን ቅሬታቸውን ለእኔ አላቀረቡም” ብለዋል።
አያይዘውም ከዚህ በፊት ቅሬታ በሚያቀርቡበት ሰዓት ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመነጋገር ብንፈቅድላቸው የሚያስከትለውን ጉዳት ለተማሪዎቹ በማስረዳት ተስማምተው እንደነበር ገልፀዋል።
አክለውም 9 ሰዓት እንዲከፈትላቸው ያልተደረገው የትምህርት ሰዓት በመሆኑ ነው፤ ምሳ ሰዓት ላይ በእቃቸው ማውጣት እንዳይችሉ የተከለአለው ደግሞ የምግብ መመረዝ እና በዶርማቸው ውስጥ በሚያስቀምጡበት ሰዓት ስለሚቀዘቅዝ ለጤንነታቸው በማሰብ ስለመሆኑ አንስተዋል።
“በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ነጠላ ለብሶ መንቀሳቀስ ተከልክሏል፣ ነገር ግን ከግቢ ሲወጡ እና ሲገቡ በላስቲክ ይዘው እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል። ” ያሉት ፕረዚዳንቱ “ይህ የሆነበትም የሌሎች እምነት ተከታዮች የተለያዩ እምነት ነክ ቲሸርቶችን ለብሰው ሌላ አጀንዳ እየፈጠሩ ስለሆነ ለተማሪዎች ደህንነት በማሰብ ነው” ብለዋል።
ከተማሪዎች መታሰር እና ሌሎች ቅሬታዎች መኖራቸውን ጥያቄ ያቀረብንላቸው ፕረዚዳንቱ “በግቢው ውስጥ እኔ ሳላውቃቸው የተፈጠሩ ችግሮች ካሉ አሁንም ቢሆን የተማሪዎችን መብት ለመጠበቅ እንሰራለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ገናናው ጎፌ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃልም “ያቀረቡት ሁሉ ቅሬታ ትክክል አይደለም እኔ እስካሁን እንደዚህ አይነት ችግሮች መኖራቸውን አልሰማሁም። ካሉ ግን እንፈታለን። በግሌም በማጣራት እሰራለሁ” ብለዋል።
ፕረዝዳንቱ ይህንን ይበሉ እንጂ ተማሪዎቹ በጥያቄዎቻቸው ቢገፉ ቅሬታ ሲያቀርቡ ከነበሩት ተማሪዎች መካከል ሊባረሩ የሚችሉ ተማሪዎች ይኖራሉ የሚል ሥጋት እንዳላቸው ግን ገልጸዋል።