ሱማሊያ፣ ፍልስጤማዊያንን ለማስፈር ከአሜሪካና እስራኤል ጋር እየተነጋገረች ነው በሚል የወጣውን ዘገባ ማስተባበሏን ሮይተርስ ዘግቧል። የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አሕመድ ፊቂ፣ ሌሎች ሕዝቦችን ሱማሊያ ግዛት ውስጥ የማስፈር ሃሳብን ፈጽሞ አንቀበለውም ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ፊቂ፣ ፍልስጤማዊያን በመሬታቸው ላይ በሰላም እንዳይኖሩ የሚያደርግን ማናቸውም ሃሳብ ሱማሊያ ውድቅ ታደርገዋለች ብለዋል ተብሏል። ሱማሊያ ይህን አቋሟን የገለጠችው፣ የአሜሪካ እና እስራኤል ባለሥልጣናት የጋዛ ፍልስጤማዊያንን አፍሪካ ውስጥ ለማስፈር ከሱማሊያ፣ ሶማሌላንድና ሱዳን ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገረች መኾኗን ዓለማቀፍ የዜና ምንጮች መዘገባቸውን ተከትሎ ነው። የሶማሌላንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴርም፣ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከአሜሪካና እስራኤል ጋር ምንም ግንኙነት እንዳልተደረገ መናገሩን የሮይተርስ ዘገባ ጠቅሷል።