የእስራኤል ወታደሮች ሁለት ኢትዮጵያዊያንን ገደሉ

የእስራኤል ወታደሮች፣ ትናንት ከዮርዳኖስ አቋርጠው ወደ እስራኤል የገቡ ሁለት ኢትዮጵያዊያንና አንድ ኡጋንዳዊ ተኩሰው መግደላቸውን የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ወታደሮቹ የተሠጣቸው ትዕዛዝ የማስጠንቀቂያ ተኩስ እንዲተኩሱ እንደነበር ዘገባዎቹ አመልክተዋል። በርካታ ጥገኝነት ጠያቂዎችና የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ከዮርዳኖስ ወደ እስራኤል እንደሚገቡና ድንበር ጠባቂ ወታደሮች እንዲመልሷቸው ሥልጣን እንደተሠጣቸው ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ወታደሮቹ ግድያውን የፈጸሙት፣ ማቾቹ “ስጋት የሚደቅን” እንቅስቃሴ በማድረጋቸው እንደኾነ የአገሪቱ መከላከያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል ተብሏል። አንድ ኢትዮጵያዊን ጨምሮ አምስት የውጭ ዜጎች ደሞ ታስረው ወደ ዮርዳኖስ እንዲመለሱ እንደተደረጉ ተገልጧል።