ኦብነግ፣ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ከቻይናው የነዳጅ ኩባንያ ፖሊ- ጅ ሲ ኤል ጋር የክልሉን የተፈጥሮ ጋዝ ለማውጣት ያለመ ስብሰባ አድርጓል በማለት ወቅሷል። ኩባንያው በኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ በማውጣት እንዳይሠማራ ያስጠነቀቀው ግንባሩ፣ ኩባንያው ከሱማሌ ክልል ሕዝብ ይኹንታ ውጭ የተፈጥሮ ጋዝ በማውጣት ሥራ ከተሠማራ ለሚፈጠረው ችግር ሃላፊነቱን ይወስዳል ብሏል። ኦብነግ፣ በክልሉ የማዕድን ቢሮና በኩባንያው መካከል ሰሞኑን የተደረገው ምክክር፣ ያልተፈቱ የሶማሌ ሕዝብ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ቸል በማለት የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝን በድብቅ ለማውጣት ያለመ ነው ብሏል። መንግሥት የተፈጥሮ ጋዙን ለመመዝበር ሲል፣ ከስድስት ዓመት በፊት አሥመራ ላይ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ቀልብሶታል በማለት ኦብነግ ከሷል። ኦብነግ፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት የተፈጥሮ ጋዙን ለማውጣት የሚያስችል ሥልጣን የለውም፤ የሱማሌ ክልል መንግሥትም በክልሉ ሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት የለውም ብሏል።