🔴 “ ‘ለኮሪደር ልማት በግዴታ ከ10,000 እስከ 20,000 ብር ካልከፈላችሁ አታልፉም’ ተብለን አሶሳ ቆመናል” – የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች
➡️ “ አይመለከታችሁም መኪና አቁማችሁ ጭነቱን ሳታራግፉ ለፓሊስ አስረክባችሁ መምጣት ትችላላችሁ ” – የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኀበር
የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች “ለኮሪደር ልማት ገንዘብ ካልከፈላችሁ አታልፉም” በሚል አሶሳ ላይ እስራት ተፈጽሞባቸው መንገላታታቸውን በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል አማረሩ።
“ለኮሪደር ልማት በግዳጅ ክፈሉ” የተባሉትን የገንዘብ መጠን ሲገልጹም፣ ተሳቢ 20 ሺሕ፣ ገልባጭ 15 ሺሕ፣ ኤፍኤስአር 10 ሺሕ ብር መሆኑን አስረድተዋል።
“የሚደርስብን ዘርፈ ብዙ ግፍ መፍትሄ የሚሰጠው መቼ ነው? ስራችንን እናውቁምና ልመና እንውጣ?” ሲሉ በምሬት ጠይቀዋል።
“በሹፌሮች የሚደርሰው ግድያና የኮቴ ክፍያ ሊቆምልን ሲገባ ይባስ ብሎ ይህን ያክል በ3 ወራት እንኳ የማናገኘው ገቢ ክፈሉ መባሉ ሕገ ወጥነት ነው” ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት ወደ አሶሳ ከተማ ፓሊስ መምሪያ ሙከራ ቢያደርግም ለጊዜው ስልክ ለማንሳት ፈቃኛ አልሆኑም።
በተጨማሪም ቅሬታው ሰምቶ እንደሆን በሚል የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኀበርን የጠየቅን ሲሆን፣ ማኅበሩ ቅሬታው እንደደረሰው ገልጿል።
የማኀበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ በሰጡን ቃል፣ “ይህን በተመለከተ ተደውሎልኝ፣ ሹፌሮቹን ምንም አይመለከታችሁም ብትፈልጉ መኪና አቁማችሁ ጭነቱን ሳታራግፉ ለፓሊስ አስረክባችሁ መምጣት ትችላላችሁ” እንዳሏቸው ገልጸዋል።
“ ለኮሪደር ልማት እናንተ በዬሄዳችበት ሁሉ አትከፍሉም። ሹፌር ብር የለውም። መጠየቅ ካለበት ባለሃብቱ ይጠየቅ ” ሲሉ አክለዋል።
አቶ ሰለሞን፣ የከባድ መኪና አሽከርካሪ “4000 ብር ነው ደመወዙ። ከየት ይመጣል?” ሲሉ ጠይቀው፣ “ይህን ለትራንስፓርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ነግረናል” ብለዋል።
“ይሄ ብቻ አይደለም። ደብረ ማርቆስ ላይ ማዳበሪያ የጫኑ ሹፌሮችን በመኪና ሚዛን መለካቱን ትተው ‘በወፍጮ ቤት ሚዛን እየተለካ ነው የምንረከባችሁ ብለዋል’ ” ሲሉ እየደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ገልጸዋል።