” ከኤርትራ መንግስት ግንኙት አላችሁ የሚል ወሬ በሬ ወለደ ውሸት ነው ” – ጉባኤ ያካሄደው ህወሓት 

” ከኤርትራ መንግስት ግንኙት አላችሁ የሚል ወሬ በሬ ወለደ ውሸት ነው ” – ጉባኤ ያካሄደው ህወሓት 

➡️ ” የኤርትራ መንግስት የያዘው ትግራይ መሬት የለም ” – የኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣን 

ጉባኤ ያካሄደ ህወሓት ምክትል ሊቀ-መንበር ኣማኒኤል ኣሰፋ ” ‘ በትግራይ መፈንቅለ መንግስት ተካሂደዋል ‘ የሚባለው ፍፁም ውሸት ነው ፤ ህወሓት በጊዚያዊ አስተዳደሩ ያለውን የስልጣን ድርሻ ከማስተካከል የዘለለ አንዳች የወሰደው እርምጃ የለም ” አሉ።

” ህዝቡን በተዘባ ወሬ ወደ አላስፈላጊ ውዥንብር በማስገባት መሬት ላይ በሌለ ግጭት ውጥረት ውስጥ ማስገባት ሃላፊነት ከሚሰማው ፓለቲከኛ የሚጠበቅ አይደለም ” ሲሉም ተናግረዋል።

” ህዝቡ የሚያሰጋ ነገር በሌለበት ሁኔታ ገንዘብ ከባንክ ለማወጣትና አስቤዛ ለመገዛት መሯሯጥ አይገባውም ” ሲሉ ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ባለው ሁኔታ ነዋሪዎች ጦርነት ይቀሰቀሳል በሚል በስፋት ከባንክ ገንዘብ እያወጡ አስቤዛም በስፋት እየገዙ ይገኛሉ።

አቶ አማኒኤል ፤ ” ህወሓት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት ለፌደራሉ መንግስት የሰጠው እውቅናን በማጠናከር በመመካከር መስራቱን ይቀጥላል ” ያሉ ሲሆን ” ፓርቲው ባነሳቸው የጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ምትክ ከፌደራል መንግስት በመተማመን አዲስ ፕሬዜዳንት ይመርጣል ” ሲሉ ተናግረዋል።

” ህወሓት የትግራይ ሰራዊት በማያሳምን መንገድ ለመበታተን የሚደረግ ሴራ እንጂ DDR መተገበርን አይቃወምም ” ያሉት ምክትል ሊቀ-መንበሩ ፤ ” ፕሬዜዳንት ነበር ” ሲሉ የጠሩዋቸው አቶ ጌታቸው ረዳ በከፍተኛ የሰራዊት አመራሮች የወሰዱት እርምጃ ” በሌለ ስልጣን የተደረገና ተቀባይነት  የሌለው ” ሲሉ አጣጥለውታል።

አቶ አማኒኤል የተወሰኑ የህወሓት አንጃዎች ከሻዕቢያ ጋር  ግንኙነት አላቸው በሚባለው ጉዳይ ” ከኤርትራ መንግስት ጋር ግንኙት አላችሁ የሚል ወሬ በሬ ወለደ ውሸት ነው ” ሲሉ መልሰዋል።

” ከኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ውጪ የሚካሄድ ግንኙነት የለም ”  ሲሉም አክለዋል።

በኤርትራ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ስለሚገኙ የኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ቦታዎች ምንም ያሉት ነገር የለም።

በተያያዘ ” የኤርትራ መንግስት የያዘው የትግራይ መሬት የለም ” ሲሉ አንድ የኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣን ፅፈዋል። 

ባለስልጠኑ የማነ ገ/መስቀል  ” ይድረስ ለግጭት ጠማቂዎች ” በሚል በX ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ” የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መተግበርና አለመተግበር የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እንጂ ኤርትራ አይመለከትም ” ብለዋል።  

” የህወሓት መከፋፈል ኤርትራን አይመለከትም ” ያሉት ባለስልጣኑ ” የትግራይ ህዝብ የውስጥ ሰላም እንዲበጠበጥ ኤርትራ ምንም ዓይነት ፍላጎት የላትም ” ብለዋል።

” የተለያየ የፓለቲካ እሳቤ ያላቸው የኢትዮጵያ ፓለቲከኞች የቀይ ባሀርን አጀንዳ እንደ አዲስ በማቀጣጠል የአፍሪካ ቀንድን ለሌላ ተጨማሪ ውጥረት ከማስገባት እንዲቆጠቡ ” በማለትም ባለስልጣኑ በX ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ አሳስበዋል።

ባለስልጣኑ ይህን ይበሉ እንጂ  የኤርትራ ሰራዊት በኢትዮጵያ የትግራይ የደንበር አከባቢ በርካታ ቦታዎች ይዞ ይገኛል።

በርካታ በትግራይ ምስራቃዊ ፣ ማእከላዊ ሰሜን ምዕራብ ዞን የሚገኙ ቀበሌ ገበሬ ማህበራት በኤርትራ ወታደሮች ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ደጋግሞ የዘገበው ቲክቫህ  ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ አሁንም በመሬት ላይ የተለወጠ አዲስ ነገር እንደሌለ የአከባቢው ነዋሪዎች በመጠየቅ አረጋግጧል።