ፌደራል መንግስቱ በትግራይ ክልል የሚታየውን ውጥረት በአስቸኳይ ሊያስቆም ይገባል፣ ዘላቂ መፍትሔም ያስፈልገዋል! (ኢዜማ)

ፌደራል መንግስቱ በትግራይ ክልል የሚታየውን ውጥረት በአስቸኳይ ሊያስቆም ይገባል፣ ዘላቂ መፍትሔም ያስፈልገዋል!

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ከፕሪቶሪያው ሥምምነት መፈጸም በኋላ አንጻራዊ ሰላም እየታየበት የነበረው የትግራይ ክልል ሁኔታ የፌደራል መንግሥቱ በፕሪቶሪያ ሥምምነት መሠረት ታጣቂ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ፣ አካታች የሆነ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት አለመመስረቱን ተከትሎ ህወሓት የእርስ በእርስ ፍትጊያ ውስጥ ገብቶ በትግራይ ክልል ውጥረት መንገሱን ይገነዘባል፡፡ በእርግጥ ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠር በመስጋት የፕሪቶሪያ ስምምነት በአግባቡ ተተግብሮ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ደጋግመን ያቀረብነውን ማሳሰቢያ ሳይሰማ በዝምታ ያለፈው ፌደራል መንግስቱ አሁን ለተፈጠረው ቀውስ ድርሻውን መውሰድ እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል፡፡

ኢዜማ በፓርቲው የውስጥ ጉዳይ ላይ የትኛውንም አስተያየት የመስጠት ፍላጎቱ የለውም፡፡ ሆኖም በህወሓት ውስጥ የተፈጠረውን የውስጥ የስልጣን ሽኩቻ ተከትሎ በክልሉ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች እየሄዱበት ያለው ግትር፣ ግጭት ቀስቃሽ ህገወጥ እንቅስቃሴ ግን በጠቅላላው እንደሀገር በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ ንፁሀን ዜጎች ላይ የሚያመጣውን ምጣኔ ኃብታዊ፣ ማኀበራዊ ብሎም የሰላምና የደኀንነት አስከፊ አደጋ በቅጡ እንረዳለን፣ ያሳስበናልም፡፡

ትግራይ ክልል አሁን ላለበት ውስብስብ ችግር የተዳረገው መሳሪያ ማንሳትን የተሻለ አማራጭ አድርጎ በሚወስደው ህወሓት የተነሳ መሆኑ እየታወቀ አሁንም የፓርቲው አመራሮች ምንም ሳይፀፀቱ ስልጣንን ጠቅልሎ በመያዝ ግብግብ ውስጥ ገብተው ለሌላ ዙር ግጭት የሚጋበዙ ከሆነ በተለይ በትግራይ ውስጥ ያሉ ዜጎች ሊረዱት የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ ይህ ስብስብ በምንም አይነት ሁኔታ ለማኅበረሰቡ ጥቅም የቆመ እንዳልሆነ ነው፡፡ በዚህ የፖለቲካ ሥልጣን ጥምን ለማርካት በሚደረግ መገፋፋት ውስጥ ባለመሳተፍ እንዲሁም ግጭት የሚቀሰቅሰውን የትኛውንም ኃይል በግልፅ በመቃወም የክልሉ ነዋሪ በአንፃራዊነት ያገኘውን ሰላም ሊያስጠብቅ ይገባል፡፡ በተግባር መሬት ላይ በግልፅ እንደሚታየው ጥቂት ግለሰቦች የዜጎች ሰላምና ደኀንነት ሳያስጨንቃቸው የግል ሥልጣን ለመጨበጥ ህገወጥ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ሰላም ወዳድ ዜጎች ሁሉ በአንድ ላይ በመቆም ይህ ቡድን ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ማስጠንቀቅ ደግሞም የትኛውም ፀብ አጫሪ ተግባሮቹ ላይ ባለመሳተፍ የህዝብ ድጋፍ እንደሌለው ማሳየት አስፈላጊ ነው እንላለን፡፡

በተለይ የፌደራል መንግሥቱ ጉዳዩ እዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በክልሉ የተፈጠረውን ትርምስ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ሊያስቆም ሲገባ ይህን አለማድረጉ ሳያንስ አሁንም ራሱን እንደሩቅ ተመልካች በመቁጠር በጉዳዩ ላይ ተጨባጭ መፍትሔ እንዲመጣ አለመስራቱ ብሎም የፕሪቶሪያው ስምምነትን በአግባቡ እንዲፈፀም ባለማድረጉ ንፁሀን ዜጎች በህይወታቸው እና በአካላቸው ዋጋ እየከፈሉ መምጣቱ ተገቢነት የሌለው ተግባር መሆኑን አውቆ አሁንም ለጉዳዩ ተገቢ ትኩረት በመስጠት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በሚያስችል ህጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ብቻ የመንግስትነት ሚናውን እንዲወጣ እናሳስባለን፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)
መጋቢት 05/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ