ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ፖለቲከኞች በቀይ ባሕር ዙሪያ የሚሠጧቸው ጠባጫሪ መግለጫዎች አላስፈላጊ ውጥረት እየፈጠሩ ነው

የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ፖለቲከኞች በቀይ ባሕር ዙሪያ የሚሠጧቸው “ጠባጫሪ መግለጫዎች አላስፈላጊ ውጥረት እየፈጠሩ ነው” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ከሰዋል። የማነ ይሄ ዓይነቱ ድርጊት በጽኑ ሊወገዝ የሚገባው እንደኾነ ገልጸዋል። የማነ፣ አንዳንድ አካላት የኤርትራ ጦር አኹንም በትግራይ ግዛቶች ውስጥ ይገኛል የሚል የሐሰት ክስ የሚያሠሙት “ግጭት ለመቀስቀስ” ለሚፈልጉ ነው በማለትም ወቅሰዋል። ኤርትራ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የኾነውን የፕሪቶሪያውን የግጭት ማቆም ስምምነት የማኮላሸት ፍላጎት እንደሌላት ያረጋገጡት የማነ፣ በተመሳሳይ ኤርትራ በትግራይ የተለያዩ ቡድኖች መካከል ያለውን ሽኩቻ የማባባስ ፍላጎት የላትም ብለዋል።