የከንቲባ ፅሕፈት ቤት የ104.4 የመቐለ ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በሚመሩት ህወሓት ቁጥጥር ስር ውለዋል።

100 ቀናት በላይ ዝግ የነበረው የመቐለ ከተማ የከንቲባ ፅሕፈት ቤት ተከፍቶ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመሩት ህወሓት የመደባቸው ከንቲባ ገብተውበታል።

የምስራቃዊ ዞን እና የዓዲግራት ከተማ ከተማ አስተዳደሮችም እንዲሁ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በሚመሩት ህወሓት ቁጥጥር ስር ውለዋል።

በደቡባዊ ምስራቅ ዞን ዓዲጉዶም ፣ የሳምረ ፣ እንዲሁም የሃገረ ሰላም ከተሞች የጊዚያዊ አስተዳደሩ መዋቅሮች በህወሓት ተመራጮች መተካታቸው ተገልጿል።

ጉባኤ ያካሄደው ህወሓት የሾማቸው የመቐለ ከንቲባ ረዳኢ በርሀ (ዶ/ር) ፤ የምስራቃዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ፍስሃ ሃይላይ ዛሬ መጋቢት 4/2017 ዓ.ም በህዝብ ታጅበው ወደየ ፅህፈት ቤቶቻቸው መግባታቸው አስታውቀዋል።

የዓዲግራት ከተማ የከንቲባ ፅህፈት ቤት ደግሞ ትናንተ መጋቢት 3 /2017 ዓ.ም የህወሓት ተመራጩ ከንቲባ ገብቶ ስራ መጀመሩ አስታውቀዋል።
 
ድርጊቱን ያወገዙት በጊዚያዊ አስተዳደሩ የተሾሙ የመቐለ ከንቲባ ብርሃነ ገ/የሱስና የምስራቃዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሰለሙን ትኩእ ፤ ህገ-ወጥ ተግባሩ የፕሪቶሪያ የሰላም ውል የሚፃረር በመሆኑ ከማውገዝ ባለፈ እስከ መጨረሻው እንደሚታገሉት በመግለፅ ወጣቱ ከግጭት ርቆ ተደራጅቶ እንዲታገል መልእክት አስተላልፈዋል።

የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ እና የማእከላይ ዞን አስተዳደሮችም ” ጉባኤ አካሂጃለሁ ” ባለው ህወሓት ቁጥጥር ስር ከዋሉ ወራት ተቆጥረዋል። 

የትግራይ ደቡባዊ ዞን ከተሞች እስከ አሁንዋ ሰዓትና ደቂቃ በጊዚያዊ አስተዳደሩ ሹመኞች እጅ ይገኛሉ። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዜዳንት ጌታቸው ረዳ የሚገኙባቸው በርካታ የጊዚያዊ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸው የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ ምንጮች ገልፀዋል። የ104.4 የመቐለ ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያ በደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በሚመራው ህወሓት በተመደቡ የመቐለ ከተማ አመራሮች አባላት ቁጥጥር ስር መዋሉ ተሰምቷል።

አመራሮቹ በሰራዊት ታጅበው ሬድዮ ጣቢያውን እንደተቆጣጠሩት ተነግሯል።

ምናልባትም በቀጣይ ደግሞ የድምፂ ወያነ እና ትግራይ ቴሌቪዥን ሚድያዎችን ሊያዙ እንደሚችሉ የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ ከታማኝ ምንጮች ለመስማት ችሏል።

መገናኛ ብዙሃኑ ዛሬ ከአዲስ አበባ የተሰጠውን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን መግለጫ እስካሁን አላስተላለፉም።