የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዕርዳታ ማቋረጡን ተከትሎ፣ በትግራይ ለ1 ሚሊዮን ዜጎች ዕርዳታ የሚያቀርቡ የረድኤት ድርጅቶች ዕርዳታ ማከፋፈል እንዳቆሙ አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል። ለአብነትም፣ ከመቀሌ ወጣ ብሎ በሚገኝ 20 ሺሕ ተፈናቃዮች የያዘ መጠለያ የምግብ ዕርዳታ እንደተቋረጠ ዘገባው ጠቅሷል። የረድኤት ድርጅቶች ጥምረት፣ ባሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ የምግብ እርዳታ ለማጓጓዝ ለነዳጅና ለጭነት ተሽከርካሪዎች ኪራይ የሚኾን ገንዘብ እንደሌለው መናገሩን ዘገባው ጠቅሷል። በገንዘብ እጥረት ሳቢያ፣ 300 ሺሕ ተረጂዎችን ላንድ ወር መመገብ የሚችል 5 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የእርዳታ ማሽላ መቀሌ መጋዘን ውስጥ እንደታሸገ መኾኑን መረዳቱንም ዘገባው ጠቅሷል። ለሳንባ ነቀርሳ፣ ኤች አይ ቪ እና በጦርነቱ ወቅት የጾታዊ ጥቃት ሰለባ በኾኑ ሴቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችም ሥራቸውን አቋርጠዋል ተብሏል።